ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዘመናዊ ሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክት የሲቪል ምህንድስና ስራ 50 በመቶ ተጠናቋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ዘመናዊ ሕንጻ ግንባታ ሲቪል ምህንድስና ስራ 50 በመቶ መድረሱን የግንባታው ተቋራጭ አስታወቀ።

የተንቀሳቃሽ መድረክ ግንባታ ስራውን ለማከናወን ዓለም አቀፍ ጨረታ መውጣቱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጥቅምት 30 ቀን 1948 ዓ.ም ተመርቆ ስራውን የጀመረ ሲሆን ላለፉት 65 ዓመታት የተለያዩ የቴአትር ስራዎች እየቀረቡበት ይገኛሉ።

የቴአትር ቤቱ የመጀመሪያ ተውኔት "ዳዊትና ኦርዮን"  ሲቀርብ 1 ሺህ 264 ተመልካቾች ተገኝተው እንደተመለከቱት መረጃዎች ያመለክታሉ።

አዲሱ ሕንጻ ከነባሩ ቴአትር ቤት ጎን በ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ይገኛል።  

የግንባታው ተቋራጭ የፌደራል መንግስት ሕንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ዘሃራ አብዱልሃዲ የአዲሱ ሕንጻ ግንባታ የተንቀሳቃሽ መድረክና ሲቪል ምህንድስና ስራዎችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ከግንባታው ስራ የተንቀሳቃሽ መድረኩ 82 በመቶ እንደሚይዝና የሲቪል ምህንድስናው 18 በመቶ እንደሚሸፍን አመልክተዋል። 

በዚሁ መሰረት የሲቪል ምህንድስና ግንባታው 50 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።

የተንቀሳቃሽ መድረክ ስራውን ለማከናወን ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ ተጫራቾች ፍላጎታቸውን ማሳወቃቸውን ጠቅሰው ከአንድ ወር በኋላ ግንባታውን የሚያከናውነው አካል ይፋ ይደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ኢንጂነር ዘሃራ ያስረዱት። 

የግንባታ ስራውን እስከ የካቲት 2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ተንቀሳቃሽ መድረኩን ጨምሮ አጠቃላይ የአዲሱ ሕንጻ ግንባታ ዓለም አቀፍ የቴአትር ቤት መስፈርቶችን እንዲያሟላ ተደርጎ የሚገነባ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የአዲሱ ብሔራዊ ቴአትር ፕሮጀክት አርክቴክትና ኮንሳልታንት አዲስ መብራቱ፤ በኢትዮጵያ መብራትን ጨምሮ ለመድረክ ስራው የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን እውቀት ውስን መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ዓለም አቀፍ ልምድ ለማግኘት በጣልያን ሚላን ከተማ የሚገኘውን "ቴአትሮ አላስካላ" የተባለውን የኦፔራ ማሳያ አዳራሽ በመጎብኘት ተሞክሮ ተወስዶ የቴአትር ቤቱ ዲዛይን ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።

ጉብኝቱ ቴአትር ቤቱ በኦፔራ ደረጃ ያሉ ትወናዎችን ሊያካሄድ የሚያስችል የመድረክ ዲዛይን እንዲሰራለት ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ ለኪነ-ጥበቡ ባለሙያዎች የተሻለ የመድረክ አጠቃቀምን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም ነው የፌደራል መንግስት ሕንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ዘሃራ አብዱልሃዲ የተናገሩት።


 

የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ልምድ ከማግኘት አኳያ ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ዘመናዊ ሕንጻ ግንባታ በ6 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ግንባታው ከምድር በታች ሁለት ወለል ያለውና ባለ 11 ወለል ከፍታ እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ከፌደራል መንግስት ሕንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም