አየር መንገዱ ያከናወነው የአውሮፕላን ግዥ ስምምነት የተቋሙን ታላቅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ግዙፍ ኢንቨስትመንት ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ያከናወነው የአውሮፕላን ግዥ ስምምነት የተቋሙን ታላቅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ግዙፍ ኢንቨስትመንት ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያከናወነው የአውሮፕላን ግዥ ስምምነት የተቋሙን ታላቅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ግዙፍ ኢንቨስትመንት መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአሜሪካው የቦይንግ ኩባንያ 67 አውሮፕላኖችን እንዲሁም ከኤርባስ ኩባንያ ጋር 11 የኤርባስ አውሮፕላኖች ግዥ ለመፈጸም ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወቃል፡፡
ይህም አየር መንገዱ እስካሁን ካከናወናቸው ኢንቨስትመንቶች ትልቁ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአውሮፕላን ግዥ ስምምነቱ አየር መንገዱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2035 ለመድረስ ያስቀመጠውን ራዕይ መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ የ67 አውሮፕላኖች ግዥ ስምምነት መፈጸሙን ጠቅሰው፤ ስምምነቱ የተቋሙን ታላቅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ግዙፍ ኢንቨስትመንት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይህም ከኢትዮጵያ ባሻገር ለአፍሪካ ትልቅ ኩራት መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
አየር መንገዱ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራእይ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ ይህን እውን ለማድረግ ተጨማሪ 100 አውሮፕላኖችን የመግዛት እቅድ መያዙን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ 67ቱ ከቦይንግ ኩባንያ መታዘዛቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም ውስጥ የ11 ቦይንግ 787-900 ድሪም ላይነር እንዲሁም የ20 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በቀጥታ ግዥ ተፈጽሞባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ቀሪ 36 አውሮፕላኖች ደግሞ በሂደት በ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ አየር መንገዱ የሚቀላቀሉ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም አየር መንገዱ ከኤርባስ ኩባንያ ጋር 11 የኤርባስ አውሮፕላኖች ግዥ ለመፈጸም ስምምነት ላይ መድረሱን ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ 145 አውሮፕላኖች እንዲሁም 135 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት፡፡