ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ መሆኑን አገራት በቅጡ ሊገነዘቡት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ ።

ከባህር በር በቅርብ ርቀት ላይ እያለች የወደብ ተጠቃሚነትን የተነፈገችው ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ እየከፈለች እስካሁንም ዘልቃለች።

የምጣኔ ኃብቷ እያደገና የሕዝብ ቁጥሯም እየጨመረ የመጣ በመሆኑ የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ሆኗል።

ከቀናት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቢዝነስ ሕግን መሰረት ያደረገና የማንንም አገር ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚጋፋ አለመሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከጎሮቤቶቿ ጋር ያላትን መልካም ጉርብትናና ወዳጅነት ተጠቅማ እንዲሁም ዓለም አቀፍ መርሆችን በመጠቀም በሰጥቶ መቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ጥያቄዋን ማቅረቧን ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወደብ የማግኘት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የባህር በር ጥያቄዋን በድርድር በሰጥቶ መቀበልና በሰላማዊ አማራጭ የዲፕሎማሲ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ከራስ ጥቅም አልፎ ለቀጠናው አገራት ዘላቂ ሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያ ለአካባቢው አገራት ሁለንተናዊ ትብብርና የልማት ትስስር እየሰራች መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ምስጋኑ የባህር በር ጥያቄዋም በጋራ የመልማት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። 

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መልካም ጉርብትናን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን፣ አጋርነትንና ትብብርን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በዚሁ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ጎረቤት አገራትም ይሁን አጠቃላይ የአለም አገራት በአዎንታዊ መልኩ ሊረዱት ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ በአካባቢው በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ መሆን አለባት ሲሉም አንስተዋል።

በቀይ ባህር አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ መንገድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ መሆኑን ገልጸው በአካባቢው የሚደረግ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ያገለለ ሊሆን አይገባም ነው ያሉት።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የሰጥቶ መቀበልና በጋራ የመልማት ጉዳይ መሆኑን አገራት በቅጡ ሊገነዘቡት ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም