የዓለም የጥቁር ህዝቦች የታሪክ፣የቅርስና የትምህርት ማዕከል በኢትዮጵያ ሊከፈት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም የጥቁር ህዝቦች የታሪክ፣የቅርስና የትምህርት ማዕከል በኢትዮጵያ ሊከፈት ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦የዓለም የጥቁር ህዝቦች የታሪክ፣የቅርስና የትምህርት ማዕከል በኢትዮጵያ ሊከፈት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊና የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ በተመለከተ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም በዚሁ ጊዜ የዓለም የጥቁር ህዝቦች የታሪክ የቅርስና የትምህርት ማዕከል በኢትዮጵያ ሊከፈት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ በአሜሪካ ካሪቢያንና በሌሎች ዓለም ላይ ያሉ ጥቁር ህዝቦች የጥናት ምርምር ተቋማትን ያቀፈ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ በመጪው ህዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዋና መቀመጫውን ኢትዮጵያ ማድረጉን በይፋ ያሳውቃል ብለዋል።
ይሄም ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ቤት፤ አዲስ አበባ ደግሞ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚያፀና መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ መቀመጫውን አዲስ አበባ እንዲያደርግ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸው፤ ይህም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ በቀኝ ግዛት ያልተያዘች፣ የስልጣኔ ማዕከል መሆኗ ለማዕከሉ መቀመጫነት እንድትመረጥ አድርጓታል ብለዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ያላት፣ እንደ ፖስታ ማህበር፣ የገለልተኛ ሀገሮች ንቅናቄ፣ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና መሰል ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች መስራች መሆኗም ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል ነው ያሉት፡፡
የማዕከሉ መቀመጫ በአዲስ አበባ መከፈት ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ላበረከተችው ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የማእከሉ መከፈት ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።