በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች የመከላከልና የቁጥጥር ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች የመከላከልና የቁጥጥር ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች የመከላከልና የቁጥጥር ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
በምስራቅ አፍሪካ የወባ ወረርሽኝ በተለይም እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ከፍተኛ የጤና ችግር መሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአፍሪካ በዚሁ የእድሜ ክልል ከሚገኙት መካከል በየአመቱ በአማካይ 600 ሺህ ህፃናት ለሞት የሚዳረጉ ሲሆን በዓለም ላይም 61 በመቶ ህፃናት በወባ ምክንያት ለሞት የሚዳረጉ መሆኑን የወርልድ ማሌሪያ ሪፖርት ያመለክታል።
በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራ እና ትግራይ ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም በጋምቤላ እና ቢኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ወባ በስፋት የሚከሰትባቸው አካባቢዎች ናቸው።
በመሆኑም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመንግስት ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር ዐቢይ አህመድ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ መግለፃቸው ይታወሳል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን፤ የወባ ስርጭት የቅድመ መከላከል እና የመቆጣጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በሽታውን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት የወባ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች እስካሁን 20 ሚሊየን አጎበሮች የተሰራጩ ሲሆን የቤት ውስጥ ኬሜካል ርጭትም ተደርጓል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ስርጭትን የመከላከልና የቁጥጥር ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑንም ዶክተር ህይወት ገልጸዋል።
ለወባ ወረርሽኝ መስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን የጠቀሱት ዶክተር ሕይወት ከዚህም ያለፈ ተጽእኖ አለው ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት የወባ ወረርሽኝን ጨምሮ ውሃ ወለድ በሽታዎችና ሌሎችም ተዛማጅ ችግሮች በዚሁ ሳቢያ ስለመባባሳቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሌ፤ የወባ ስርጭትን ለመከላከል በመንግስት የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ የህብረተሰቡ ጥንቃቄም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የመኝታ አጎበሮች ስርጭት ቢኖርም በህብረተሰቡ ዘንድ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ለመከላከል ሂደቱ እንቅፋት በመሆኑ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የተከሰተውን የኩፍኝና የኮሌራ በሽታ ለመከላከል የተደረገው ጥረትም ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ዶክተር መሳይ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የጤና ጉዳይን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ የወባ በሽታ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ29 አገራት መከሰቱን መግለፃቸው ይታወሳል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል የአጎበር ስርጭትን ጨምሮ የኬሚካል ርጭትና ተያያዥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።