ቀጥታ፡

ትልልቅ ሀገራዊ የጤና ግቦችን ለማሳካት ኢትዮጵያ የጤና ቴክኖሎጂዎችን እና ኢኖቬሽኖችን ማዕከል አድርጋ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦እንደሀገር ያስቀመጥናቸውን ትልልቅ ሀገራዊ የጤና ግቦች ለማሳካት ኢትዮጵያ የጤና ቴክኖሎጂዎችን እና ኢኖቬሽኖችን ማዕከል አድርጋ እየሰራች መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በህንድ፣ ቪዛግ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው አለምአቀፍ የጤና ፈጠራ ፎረም (World Health innovation fourm -2023) ላይ የኢትዮጵያ ቡድን እየተካፈለ ይገኛል ፡፡


 

በፎረሙ የኢትዮጵያ ቡድን ከአለም ጤና ድርጅት የልዑክ ቡድን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራትና የአለምአቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በትብብር ስራዎች ዙርያ ውይይት እያደረገ ይገኛል። 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ  ዶ/ር አየለ ተሾመ ከአለም ጤና ድርጅት የኢኖቬሽን ሀብ ዳይሬክተር ሉዊስ አገርስናፕ እና አባላቱ ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት እንደተናገሩት ኢትየጵያ የጤና አገልግሎቶችን ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል ቴክኖሎጂንና ፈጠራን ማዕከል አድርጋ እየሰራች ያለውን ተግባራት አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉን አቀፍ የፈጠራ ስራን ለማበረታታት በፖሊሲ፣ በስትራቴጂና በመዋቅር በመደገፍ በመንግስት የጤና አገልግሎቶችን ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል የሰጠውን ትኩረትም  አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለዜጎች የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂና በኢኖቬሽን ለማስደገፍ ከመዋቅራዊ ዝግጅት ጀምሮ በሰው ሃይል አቅም ግንባታ እየተሰራ እንደሆነም ዶ/ር አየለ አብራርተዋል።

 

አሁን ላይ ወጣት የፈጠራ ባለቤቶችን፣  የፈጠራ እውቀቶችን ወደ ምርት አስገብቶ የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል አልፎም የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታት መንግስት የዘረጋውን ምቹ ሁኔታዎች መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ባለድርሻ አካላትና የግሉ ዘርፍ ተዋንያኖች በስፋትናተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትር ዴኤታው ጠይቀዋል።

የአለም ጤና ድርጅት የኢኖቬሽን ሀብ ዳይሬክተር ሉዊስ አገርስናፕ ኢትዮጵያ የጤና ስርዓቱን በቴክኖሎጂ እና በኢኖቬሽን ስራዎች ለማገዝ የምታከናውነውን ተግባር  አድንቀዋል፡፡

በቀጣይ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ጤና ተቋማት የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን በፈጠራ ስራዎች ለመደገፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉና በትብብር እንደሚሰሩ መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም