በህንድ ዋሻ ውስጥ የሚገኙ 40 ዜጎችን ለመታደግ የነብስ አድን ሰራተኞች ቁፋሮ ሊጀምሩ ነው

137

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦በህንድ በተደረመሰ ዋሻ ውስጥ የሚገኙ 40 የግንባታ ሰራተኞችን ለመታደግ የነብስ አድን ሰራተኞች ቁፋሮ ሊጀምሩ እንደሆነ የሰሜናዊ ህንድ መንግስት ገልጿል።

በሰሜናዊ ህንድ አርባ የግንባታ ሰራተኞች በስራቸው ላይ እያሉ  የሚገኙበት ዋሻ አንደኛው ክፍል ተደርምሶ መውጫ ተዘግቶባቸዋል።

ሰራተኞቹ በመንገድ ግንባታ ላይ እያሉ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት የ 2 ነጥብ 7 ማይል ዋሻ የተወሰነ ክፍል እንዲደረመስ አድርጓል።

እስከ አሁን የነብስ አድን ሰራተኞች የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት ለሰራተኞቹ እያቀረቡ  ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት ወደ ሰዎቹ ለመድረስ በዋሻው ፍርስራሽ ውስጥ ቁፋሮ ለመጀመር መዘጋጀታቸው ተመላክቷል።

በህንድ በሰሜናዊ ግዛት የመሰረተ-ልማትና የልማት ኮርፖሬሽን ባለስልጣን አንሹ ማኒሽ ካሃልኮ የቁፋሮ ስራው ዛሬ እንደሚጀመር ነው ያሰታወቁት።

የቁፋሮ ስራዉ በፍጥነት ከተጀመረ ሰራተኞቹን ካሉበት ዋሻ ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያፋጥነው ገልጸዋል።

የነብስ አድን ሰራተኞቹ ካለፈው አሁድ ጀምሮ በዋሻ ውስጥ የተቀረቀሩ የግንባታ ሰራተኞችን ለማዳን ሰፊ የብረት ቱቦ ወደ ዋሻ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ለዚህም ለቁፋሮ የሚሆንም መሳሪያ በሶስት አውሮፕላኖች ተጭኖ ከኒው ዴሊህ መምጣቱ ተጠቁሟል።

ከሰራተኞቹ መካከል አንዳንዶቹ የህመም ስሜት እያጋጠማቸው እንደሆነ ሪፖርት ቢያደርጉም፤ እስከ አሁን የከፋ ጉዳት የደረሰበት ሰራተኛ አለመኖሩ ተገልጿል።

በነብስ አድን ኦፕሬሽኑ ከ200 በላይ የነብስ አድን ሰራተኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የግንባታ ሰራተኞቹ ቤተሰቦችና ጓደኞች ከተደረመሰው ዋሻ አካባቢ ሆነው ሁኔታውን እየተከታተሉ እንደሚገኙና የግዛቲቱ መንግሰት የነብስ አድን ስራውን ማፋጠን በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ከህንድ ጦርና ከውጭ የነብስ አድን ባለሙያዎች ጋር እየመከረ ስለመሆኑ ዘ አይሪሽ ኒውስ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም