የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የመግቢያ ነጥብን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የመግቢያ ነጥብን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በ2016 ዓ.ም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ገብተው በተለያዩ የሙያ መስኮች ስልጠና የሚወስዱ ተማሪዎች የመግቢያ ነጥብ ይፋ አድርጓል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የመቁረጫ ነጥቡን አስመልክቶ እንደተናገሩት ዜጎች ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚመጡት መሄጃ ስላጡ ሳይሆን ያላቸውን አቅም አውጥተው መጠቀም እንዲችሉ ነው፡፡
ይህም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጣሪ አቅሞች እና ተጨማሪ አማራጭ የሚሰጡ ተቋማት ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሰረት ከዚህ ቀደም እስከ ደረጃ 5 ብቻ ተገድቦ የነበረው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የእድገት መሰላል እስከ ደረጃ 8 ድረስ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡
ይህም ፖሊሲው ደረጃ ስድስትን ከመጀመሪያ ድግሪ፣ ደረጃ ሰባትን ከማስተርስ እንዲሁም ደረጃ ስምንትን ከዶክትሬት ዲግሪ ትይዩ እንዲሆን አድርጓል፡፡
ስለሆነም በዚህ ዓመት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ወደ ቴክኒክና ሙያ መግባት ቢፈልጉ በደረጃ 6 ገብተው መሰልጠን እንደሚያስችላቸው አመላክተዋል፡፡
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በደረጃ 6 የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች እንደሚስተናገዱ የጠቆሙት ሚኒስትሯ በዚህ ዓመት በተቀመጠው መስፈርት መሰረት በክልሎች አማካኝነት የሰልጣኞች ምደባ ይካሄዳል ብለዋል፡፡
በዚህም በተያዘው የሥልጠና ዘመን 632 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሥራ ገበያውን የሰው ሀይል ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ከደረጃ 1-ደረጃ 5 እንደ ውጤታቸው ተመድበው እንደሚሰለጥኑም ነው የገለጹት፡፡
በወጣው መቁረጫ ነጥብ መሰረት ደረጃ አንድ እና ሁለት 110 ሺህ 15 ፤ በደረጃ ሦሰት እና አራት 412ሺህ 557 እንዲሁም በደረጃ አምስት 110ሺህ 15 እንደሚሳተፉ የጠቆሙት ሚኒስትሯ በደረጃ ስድስት ደግሞ 2ሺህ የሚሆኑ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል፡፡
የ2016 የስልጠና ዘመን የተዘጋጀው መቁረጫ ነጥብ የ2015 ትምህርት እና የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
ከ2014 ዓ.ም በፊት ለነበሩ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ደግሞ በስልጠና ዘመኑ በነበረው መቁረጫ ነጥብ መሰረት እንደሚስተናገዱ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በ2016 ዓ.ም ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ያዘጋጀው የመግቢያ ነጥብ ከዚህ በታች ባለው ሰንጠረዥ ቀርቧል፡-