በሰሜናዊ ቻይና በአንድ ህንፃ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የ25 ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜናዊ ቻይና በአንድ ህንፃ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የ25 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦በሰሜናዊ ቻይና ሻንዚ ግዛት በአንድ የድንጋይ ከሰል አምራች ኩባንያ ህንፃ ላየ በደረሰ የእሳት አደጋ የ25 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች በአደጋው ጉዳት ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡
እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ የእሳት አደጋውን በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ አቅራቢያው ሆስፒታል በመውሰድ ተጨማሪ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።
ንብረትነቱ ዮንጁ የተባለ የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ኩባንያ በሆነው ባለ አራት ወለል ህንጻ ላይ ሌሊቱን በተነሳው ቃጠሎ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑንና የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።
ከህንፃው 63 ሰዎችን ማስወጣት የተቻለ ሲሆን 51 ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፤ የሟቾቹ ቁጥር ወደ ሆስፒታል ከሄዱት መካከል ስለመሆኑ አለመረጋገጡን ዛገባው አመልክቷል፡፡
እሳቱ ከህንፃው ሁለተኛ ፎቅ እንደተነሳ የዘገበው ደግሞ ዥንዋ የዜና ወኪል ነው፣ እንደዘገባው እሳቱ የፎቁን መላውን ክፍል ማዳረሱን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች መታየቱን ጠቁሟል።