የማሪታይም ባለስልጣን በሁሉም ዘርፎች ያሳየው አፈፃፀም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
የማሪታይም ባለስልጣን በሁሉም ዘርፎች ያሳየው አፈፃፀም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን በሁሉም ዘርፎች ያሳየው አፈፃፀም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የመጀመሪያ የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በመገምገም የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማዕከል የማስፋፊያ ፕሮጀክትንም ጎብኝቷል፡፡
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር አብዱልበር ሸምሱ፤ የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማዕከል የማስፋፊያ አጠቃላይ ፕሮጀክት ግንባታ 52 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ማስፋፊያው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅም ተርሚናሉን ስፋት አሁን ካለበት 60 ሄክታር ወደ 120 ሄክታር ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የኮንቲኔር የወደብ ላይ ቆይታ ለመቀነስ በመልቲ ሞዳል በተሰራው ስራ የቆይታ ጊዜን ወደ 9 ቀናት ማሳጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።
የበለጠ እንዲሳለጥም በነጻ የንግድ ቀጣና ለመጠቀም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም የማስፋፊያ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በሩብ ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
በግንባታ ላይ የሚገኘው ደረቅ ወደቡ ሁለገብ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማዕከል ሲጠናቀቅም የወጪና ገቢ ዕቃዎች እንዲሳለጡ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የሞጆ ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ የፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጅነር ደሳለኝ ጌታሁን በበኩላቸው የወደቡ መጠናቀቅ ለአገር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የሲቪል ስራ፣ የአይ ሲ ቲ እና ተዛማጅ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ብለዋል።
የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፤ የባለስልጣኑ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ክንውን የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በሁሉም ዘርፎች ያሳየው አፈፃፀም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ 62 በመቶ የኮንቴነር ምርቶችን ራሱ አሽጎ ወደ ውጪ መላኩን ያደነቁ ሲሆን ይህም የውጪ ምንዛሬን ወጪን ከመቀነስ አንጻር ተስፋ ሰጪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአገር ውስጥ የውሃ አካላትን ለትራንስፖርት ለማዋል በባሮ ወንዝ ላይ የተጀመረውን ስራም ወደ ሌሎች ውሃ አካላት መስፋፋት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡