የኢትዮጵያ እና ቻይናን ግንኙነትና በምክር ቤቶቻቸው መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ቻይናን ግንኙነትና በምክር ቤቶቻቸው መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የቻይና ብሔራዊ ሕዝብ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሎሳንግ ጊልትሰን ከተመራ ልዑክ ጋር ውይይት አድርገዋል።
የውይይቱ ዓላማ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልፅዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በውይይቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ቻይና የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ከቻይና ጋር በባህል ልውውጥ፣ በእህትማማች ከተሞች እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በፕሮጀክቱም መካካል በአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር፣ የተማሪዎች ስኮላርሺፕ እንዲሁም በአቅም ግንባታ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በሰላም እና በጸጥታ ጉዳዮች እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮችም በጋራ መስራት እንደምትፈልግም ጠቅሰዋል፡፡
የቻይና ብሔራዊ ሕዝብ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሎሳንግ ጊልትሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ መሸጋገሩን ተናግረዋል፡፡
የሁለቱን አገራት ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ በሁሉም ዘርፍ ያሉ ትብብሮችን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይኖርብናልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ልማትና ፈጣን እድገት በማገዝ የቻይና ጥረት የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው የቻይና እና የአፍሪካን የጋራ ትብብር ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
ውይይቱን የተከታተሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በአገራቱ ፓርላማዎች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማካሄድም ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና በመሰረተ ልማት ዘርፍ ቻይና በስፋት እየተሳተፈች መሆኑንም ገልጸዋል።
በቻይና ብሔራዊ ሕዝብ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሎሳንግ ጊልትሰን የተመራ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።
ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1970 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።