ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ የሚደረገውን ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለማስቀረት እየተሰራ ነው  

መተማ ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ሰሊጥና አኩሪ አተርን ጨምሮ ገበያ ተኮር በሆኑ ምርቶች ላይ የሚደረገውን ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ንግድ መምሪያ ገለጸ።

ሰሊጥና አኩሪ አተርን ጨምሮ ገበያ ተኮር ምርቶች የውጭ ገበያና የኢንዱስትሪዎች ግብዓት ፈቃድ ባላቸው አቅራቢዎች የሚቀርቡ ምርቶች ናቸው።

ምዕራብ ጎንደር ዞን ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙና ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ የሚውሉ የቅባት እህሎች በብዛት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

በምርቶቹ ላይ ጤናማ የሆነ የንግድ የአሰራር ሥርዓት ለመፍጠር የሚረዳ የምክክር መድረክ ዛሬ በገንዳ ውሃ ከተማ ተካሄዷል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌትነት በልሁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶች ላይ የሚታየው ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ አርሶ አደሩና ህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ጫና እየፈጠረ ነው።

ይህን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን በማካተት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥርም 30 በሚሆኑ ህጋዊ ያልሆኑ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

የተጀመረው ህግን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስረዱት ኃላፊው፤ ለዚህም በየደረጃው ግብረ ኃይል በማቋቋም ክትትልና ቁጥጥሩ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በየመንገዱ ኬላ በማዘጋጀት አርሶ አደሩንና ህጋዊ ነጋዴዎችን ለአላስፈላጊ እንግልት የሚዳርጉ ግለሰቦችና ህገ ወጥ ደላላዎች ሥርዓት እንዲይዙ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በኮኪት አንደኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል የሰሊጥ አቅራቢ አቶ ተካልኝ ይብለጥ በበኩላቸው፤ ህገ ወጥ ግብይት በሥራቸው ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።

"የእርሻ ሥራን  በኮንትራት እናከናውናለን" በሚሉ ሰዎች  የሚካሄደው ህገ ወጥ ንግድ ህጋዊ ግብይቱን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህም መንግሥት አምራቾችና ህጋዊ ነገዴዎች ወቅታዊ ገበያን ታሳቢ ያደረገ የተረጋጋ ግብይት ለመፍጠር ነጋዴዎችንና ደላሎችን እንዲከላከል ጠይቀዋል።

ግብር የማይከፍሉ ህገ ወጥ ነጋዴዎች በህጋዊ ነጋዴዎች እንቅስቃሴና በአገር ገቢ ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው  ያሉት ደግሞ የሰሊጥ አቅራቢ ነጋዴ የሆኑት አቶ ሰጠኝ አምሳሉ ናቸው።

በመሆኑም አምራቹ በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ እንዲሆንና መንግሥት ማግኘት ያለበትን ግብር በአግባቡ እንዲያገኝ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ ነጋዴዎች፣ የባንክ ሥራ አስኪያጆች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተካፍለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም