አቶ ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሪታ ላራንጂንሃ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አቶ ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሪታ ላራንጂንሃ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፦ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሪታ ላራንጂንሃን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
አቶ ደመቀ በውይይታቸው በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ መክረዋል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን አጋርነት እና ትብብር መደበኛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
በሁለቱ ወገን በኩል በየዘርፉ የሚደረግ ውይይት አስፈላጊነትን ያነሱት አቶ ደመቀ፥ ኢትዮጵያ የፊታችን ታህሳስ ወር ለሚደረገው ስብሰባ ያደረገችውን ዝግጅት በተመለከተ አስረድተዋል።
መንግስት በትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ አቶ ደመቀ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ከብሄራዊ ምክክር እና ከሽግግር ፍትህ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሪታ ላራንጂንሃ በበኩላቸው በአውሮፓ ኅብረትና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን አድንቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቷን ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት በማድነቅም የአውሮፓ ኅብረት ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።