ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ አቅም ለማሳደግና የወደብ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የባህር በር መሠረታዊ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ አቅም ለማሳደግና የወደብ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የባህር በር መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።

የምጣኔ ኃብቷ እያደገና የሕዝብ ቁጥሯም እየጨመረ የመጣ በመሆኑ የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ሆኗል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቢዝነስ ሕግን መሠረት ያደረገ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነትን የተከተለ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ የወደብ ጥያቄዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፤ ኢትዮጵያ 40 ምርጥ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ካላቸው አገራት ተርታ እንድትመደብ ለማድረግ አገራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት በተከናወኑ ተግባራት የአገሪቱን የሎጂስቲክስ ሥርዓት በማዘመንና በማሻሻል ረገድ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

በዘርፉ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም አሁንም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት የሎጂስቲክስ አፈጻጸም ዝቅተኛ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የሎጂስቲክስ አቅምን ለማሳደግና በወደብ አገልግሎት እየገጠማት ያለውን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

የባህር በር የሌላቸው አገራት የእድገት ምጣኔያቸው 20 በመቶ ወደ ኋላ ይጓተታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የዘርፉን እድገት የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የአገሪቱን አጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገት ከ25 እስከ 30 በመቶ ለማሳደግ የሚያግዝ በመሆኑ መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን አብራርተዋል።

የወደብ አገልግሎት ክፍያ በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው ይህም ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ማውጣቷን አስታውሰው፤ ከዚህ በላይ የሚባክኑ በርካታ ነገሮች እንዳሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሥራት ይገባል ያሉት አቶ ደንጌ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም