የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከቀጣናው አገራት ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዲፈጠር አድርጓል-በኬንያ እና ጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከቀጣናው አገራት ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዲፈጠር አድርጓል-በኬንያ እና ጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከቀጣናው አገራት ጋር ጠንካራ ወዳጅነትን መፍጠር ያስቻለ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው በኬንያ እና ጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ።
6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄዱ ይታወቃል።
በስብስባው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ በምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና መስፈሪያው ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት እንዲሁም መልክዓ ምድራዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶችን መነሻ በማድረግ ከሌሎች አገራት ጋር ተጋግዞና ተባብሮ መስራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፖሊሲው ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሰጠና ወደፊት የሚፈጠረውን ቀጣናዊ ትስስር ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ኢትዮጵያና ኬንያ በተለያዩ መስኮች ያላቸው የሁለትዮሽ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሁለቱ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርን ወደ ጎረቤት አገራት በማስፋት በኬንያ በ2015 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መከናወኑን አስታውሰዋል።
ከቀናት በፊት የኬንያ መንግስት 100 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ቀን እንዲተከል ባዘጋጀው ልዩ በዓል ላይ ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተሳትፎ ማድረጉን አመልክተዋል።
ኬንያ በ10 ዓመት ውስጥ 15 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ማቀዷን የገለጹት አምባሳደሩ ይህም ሁለቱ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት።
በኢኮኖሚው መስክም ኢትዮጵያና ኬንያ ባደረጉት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ከኢንቨስትመንት አኳያም የኬንያ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የተለያዩ አማራጮችን እየተመለከቱ እንደሚገኝና የሳፋሪኮም ኩባንያ በቴሌኮም ዘርፍ መሰማራቱ የዚሁ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያና ኬንያ በሰላምና ደህንነት መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙም ነው አምባሳደር ባጫ ያስረዱት።
የሁለቱ አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በተለይም በአገራቱ አዋሳኝ አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ጉርብትና ይበልጥ እየጎለበተ መምጣቱንም አንስተዋል።
ሁለቱ አገራት ወደ 35 የሚሆን በተለያዩ መስኮች መስራት የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ ስምምነቶች መፈራረማቸውን አስታውሰው መንግስት የስምምነቶቹን ትግበራ በማፈጠን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ ልዩ የሚባል ታሪካዊ ወዳጅነትና የአብሮነት ትስስር ያላቸው አገራት መሆናቸውን አመልክተዋል።
ሁለቱ አገራት ያላቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ጠቅሰው በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣በኢኮኖሚና በአረንጓዴ ልማት የዳበረ ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አብዛኛው የገቢና የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወነው በጅቡቲ ወደብ በኩል መሆኑን በማንሳት።
አገራቱ የጋራ ፍላጎቶቻቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሁለቱ አገራት ኢኮኖሚና ንግድን ጨምሮ ያላቸውን ጠንካራ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና የአገራቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው አምባሳደር ብርሃኑ ያስረዱት።
ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ በሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካኝነት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አምባሳደሮቹ ፖሊሲው ትብብርን ከማጠናከር ባለፈ ጠንካራ ወዳጅነትን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።