የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መዳረሻዎችን በማስፋት አፍሪካን ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መዳረሻዎችን በማስፋት አፍሪካን ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መዳረሻዎችን በማስፋት አፍሪካን እርስ በእርስና ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ስራውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ባንጉይ ዳግም በረራውን በዛሬው እለት በይፋ ጀምሯል።
የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ ከ2010 ጀምሮ ወደ ባንጉይ በረራ ማድረግ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ላለፉት ስምንት አመታት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዛሬው እለት ደግሞ አየር መንገዱ በአዲስ ምእራፍ ዳግም በረራውን መጀመሩን ጠቁመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መዳረሻዎችን በማስፋት አፍሪካን እርስ በእርስና ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዛሬው እለት ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ባንጉይ የጀመረው በረራ በአፍሪካ የበረራ መዳረሻዎቹን 63 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ደግሞ 135 ማድረሱን ገልጸዋል።
የባንጉይ በረራ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር ረገድ የጎላ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰው በምስራቅ ኤዥያና በመካከለኛው ምስራቅ የባንጉይን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣናው አገራት መካከል ለሚተገበረው ነፃ የንግድ ቀጣና መቀላጠፍ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በአህጉሪቷ ያሉ ዋና ዋና ከተሞችን በማገኛኘት ለአፍሪካ ነጠላ የአየር ትራንስፖርት ገበያ /SATM/ ተግባራዊነት የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የማዕከላዊ አፍሪካ አምባሳደር ፈርናንድ ኮኖ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባንጉይ ዳግም በረራ በመጀመሩ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
የበረራው መጀመር የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ትብብር ከማጠናከር ባለፈ አህጉራዊ ትስስር ለመፍጠር የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ባንጉይ በሳምንት ሶስት ጊዜ በረራ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።