የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት ከሚገነባቸው መንደሮች ትልቁን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት ከሚገነባቸው መንደሮች ትልቁን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/2016 (ኢዜአ)፦የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት በአፍሪካ ሊያስገነባቸው ካቀዳቸው 1ሺ መንደሮች ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ የጥምረቱ ሥራ አስፈፃሚ ዲያዮ ቹንሄ ተናገሩ።
በሥራ አስፈፃሚው ዲያዮ ቹንሄ የተመራ የልዑካን ቡድን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር መክሯል።
ጥምረቱ በአፍሪካ ውስጥ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በኢኮኖሚ እና ንግድ ትብብር ላይ በተሰማሩ የቻይና ኢንተርፕራይዞች በፈቃደኝነት የተቋቋመ ሲሆን በአፍሪካ የተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚ ድጋፎችንም የሚያደርግ ነው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጥምረቱ ሊገነባ ካቀዳቸው መንደሮች ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የቻይናና የኢትዮጵያን የጠበቀ ግንኙነት ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ የሴቶችናና ህፃናትን እንዲሁም የአጠቃላይ ማህበረሰቡን ህይወት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ የቻይና መንግስት እና ኢንተርፕራይዞች እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦም አመስግነዋል።
የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት ሥራ አስፈፃሚ ዲያዮ ቹንሄ ጥምረቱ ሊገነባ ካቀዳቸው 1ሺ መንደሮች ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።
የሴቶችና ህፃናት የማህበራዊ ህይወት መሻሻል ላይ ጥምረቱ ይሰራል ያሉት ስራ አስፈፃሚው ለፕሮጀክቱ መሳካት የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት በአፍሪካ ውስጥ ለማህበራዊ ህይወት መሻሻል ያግዛሉ ያላቸውን 1ሺ መንደሮችን ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡