ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በሀገር ወስጥ ከሚገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ወስጥ ከሚገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ለምክክሩ ሂደት ስኬት ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አካታችነትና አሳታፊነት መሆኑን ጠቁሞ ለዚህም የዲያስፖራውን ማህበረሰብ የማሳተፍ አስፈላጊነት ገልጿል።

የዲያስፖራው ማህበረሰብ በምክክር ሂደቱና ኮሚሽኑ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆንና እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ተገቢውን በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የመድረኩ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አስረድቷል።

የዲያስፖራ ማህበረሰቡ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱና አሁንም በተለያየ አግባብ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን መግለጫው አመላክቷል።

በመጪው ቅዳሜ ህዳር 8/ 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ለግማሽ ቀን በአዲስ ፓርክ/ ሚሊኒየም አዳራሽ/ በሚካሄደው በዚሁ የውይይት መድረክ ቁጥራቸው ከ 700 የማያንስ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

በመድረኩ ስለ ሀገራዊ ምክክር ምንነት፣ በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ያለው ሀገራዊ ምክክር አላማዎች፣ እንዲሁም የምክክሩን ሂደት የሚመራው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስከ አሁን ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራትና ዕቅዶቹ ላይ በመምከር ቀጣይ በዲያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎና ሚና ዙሪያም ውይይት እንደሚደረግ ኮሚሽኑ ገልጿል።

መድረኩ ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያካሂዳቸው የቅድመ ምክክር መድረክ አካል ሲሆን በቀጣይም ይህን መሰል መድረክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም