ልዩነትን ከሚፈጥሩ እሳቤዎች በመውጣት የሚያቀራርቡ ትርክቶችን በማጉላት ለሀገር ግንባታ መሥራት አለብን - ኢዜአ አማርኛ
ልዩነትን ከሚፈጥሩ እሳቤዎች በመውጣት የሚያቀራርቡ ትርክቶችን በማጉላት ለሀገር ግንባታ መሥራት አለብን
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፦ቅራኔና ልዩነትን ከሚፈጥሩ እሳቤዎች በመውጣት የሚያቀራርቡ የጋራ ትርክቶችን በማጉላት ለሀገር ግንባታ መሥራት አለብን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።
በትናንትናው እለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ዋነኛው ችግር አባባሽ ግን ዋልታ ረገጥ እሳቤና ነጠላ ትርክት መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም በመደማመጥና በመከባበር ለጋራ ጉዳይ በጋራ መሥራት ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ መሆኑን አመላክተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች በኢትዮጵያ አብሮነትን የሚያጠናክሩ የወል ትርክቶችን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
በየዘመናቱ በአገሪቱ በበጎም ይሁን በመጥፎ ተከስተው የነበሩ ሁነቶች በትክክለኛና በእውነተኛ መንገድ በመረጃ ተሰድረው ባለመቀመጣቸው እስካሁንም የንትርክ ምክንያት ሆነው መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ትክክለኛ የሆኑ የጋራ ታሪኮች ሕዝብን ከማቀራረብና ከማግባባት ባለፈ ለሀገር ግንባታ መሠረት በመሆናቸው ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዋና ጸሐፊ አበበ አካሉ፤ አገር በጋራ የምትቆመው አቀራራቢ የጋራ ታሪኮችን በማጉላት መሆኑን ሁላችንም ግንዛቤ መያዝ አለብን ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከሚያራርቁ እሳቤዎች በመውጣት የሚያቀራርቡ ትርክቶችን መገንባት ላይ ማተኮር አለባቸው ነው ያሉት።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ ሕዝብን ከሕዝብ የሚከፋፍሉና የግጭት ምክንያት የሚሆኑ ሃሳቦችን ማራመድ ለሀገርም ይሁን ለሕዝብ የማይጠቅም መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም የሚያቀራርቡና የጋራ የሆኑ እሴቶች ላይ በማተኮር ለሀገር ግንባታ ሁላችንም መሥራት አለብን ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አባል የሆኑት ዶክተር ከፈና ኢፋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ወደፊት መራመድ የምትችለው የሚያራርቅ ነጠላ ትርክትን በመተው የጋራ ትርክትን መገንባት ሲቻል ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ብዝኃ እሴቶች የጋራ ኃብት በማድረግ ለሀገር ግንባታና ለአብሮነት መጠናከር ልንጠቀምባቸው ይገባል ነው ያሉት።