ቀጥታ፡

የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሲከበር ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በሚያጠናክር መልኩ እንዲሆን ዝግጅት እየተደረገ ነው -- ፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዳማ ፤ህዳር 5/2016 (ኢዜአ)፡-የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ስናከብር ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በሚያጠናክር መልኩ እንዲሆን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

18ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን በማስመልከት ለትምህርት ተቋማት የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና ህገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ ባንችይርጉ መለስ፣ ''የዘንድሮው በዓል በጋራ እሴቶቻችን የተገኙ ስኬቶችን የምናጠብቅበት ነው'' ብለዋል።

''በዓሉ ሲከበር በቀጣይ የብዙሃን መብቶችን በዕኩልነት በማስተናገድ ሀገራዊ አንድነትን ይበልጥ በምናጎለብትበት መንገድ ይሆናል'' ብለዋል።

በዓሉ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጠናከር፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮች የሚታለፉ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ይከበራልም ነው ያሉት።

በሀገር ደረጃ ህብረ ብሔራዊነትን ከማጎልበት አንፃር በርካታ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም በሂደት ላይ ፈተናዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

''ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በቅድሚያ ህብረብሔራዊነትን መቀበል ያስፈልጋል'' ያሉት ወይዘሮ ባንችይርጉ ''የህዝቦች ዕኩልነትና ብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አብሮነትን የሚያጎለብቱ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት አለብን'' ብለዋል።

ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለ18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ስኬታማነት እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ተቋማቱ በህገ መንግሥት አስተምህሮና ፌዴራሊዝም ዙሪያ የተጀመረውን ንቅናቄ በማገዝ የድርሻቸውን ማበርከት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

በዚህም በዴሞክራሲ ባህልና በህገ መንግስት ዙሪያ ግንዛቤን በማሳደግ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት  በተጀመረው ጉዞ ውስጥ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ ፅሑፍ ያቀረቡት የህገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሃይለየሱስ ታዬ በበኩላቸው ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲጎለብት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

በተለይ ፌዴራሊዝምና ህገ መንግስታዊ አስተምህሮን ለትውልድ በማስረፅ ረገድ የጎላ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው ተቋማቱ ትውልዱ በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ያሉ የአስተምህሮ ክፍተቶችን መሙላት አለባቸው ብለዋል።

18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት ይከበራል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም