ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የባህር በር አማራጮችን መፈለግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው- የፓርላማ አባላት

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 5/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና አማራጭ ወደብ መፈለግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ከባህር በር በቅርብ ርቀት ላይ እያለች የወደብ ተጠቃሚነትን የተነፈገችው ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ እየከፈለች እስካሁንም ዘልቃለች።

የምጣኔ ኃብቷ እያደገና የሕዝብ ቁጥሯም እየጨመረ የመጣ በመሆኑ የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ሆኗል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በፊት የሁለት ወደብ ባለቤት የነበረች ቢሆንም አሁን ላይ የሕዝብ ቁጥሯና ኢኮኖሚዋ በብዙ እጥፍ አድጎ አማራጭ ወደብ የሌላት በመሆኑ መቸገሯን አንስተዋል።

የጅቡቲ መንግሥትና ሕዝብ ወደባቸውን እንድንጠቀም ላሳዩት አጋርነት እናመሰግናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቢዝነስ ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ ምላሽን የሚሻ እንጂ የየትኛውንም አገር ሉዓላዊነት የሚጋፋ አለመሆኑንም አብራርተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለኢትዮጵያ የባህር በር አማራጮችን መፈለግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ተሾመ ዋለ፤ የባህር በርን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ሃሳብ ዜጎችን ሁሉ የመመለከትና የጋራ እሳቤና ጥረትን ጭምር የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ከወደብ አገልግሎት ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያን እየገጠማት ያለውን ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል እሳቤን የያዘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ ከየትኛውም አገር ጋር ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከ90 በመቶ በላይ በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተሾመ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ወሳኝና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ደሳለኝ ርሶ፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለወደብ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣች በመሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሊገነባላት የሚችል ሃብት እያሳጣት ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄም የሰጥቶ መቀበልና በጋራ የመልማት ጉዳይ መሆኑን አገራት በቅጡ ሊገነዘቡት ይገባል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም