የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባንጉይ በረራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባንጉይ በረራ ጀመረ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 5/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ባንጉይ በረራ ጀመረ::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀደም ሲል ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ባንጉይ በረራ ያደርግ የነበረ ቢሆንም ተቋርጦ ቆይቷል።
በመሆኑም አየር መንገዱ ወደ ባንጉይ ዳግም በረራውን በዛሬው እለት በይፋ ጀምሯል።
የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ፤ በማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት አየር መንገዱ በተለያዩ የአለም አገራት የበረራ መዳረሻዎችን እያሰፋና የአውሮፕላን ቁጥሮችንም እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ባንጉይ የጀመረው በረራ በአፍሪካ የበረራ መዳረሻዎቹን ወደ 63 አድርሶታል ነው ያሉት።
የባንጉይ በረራ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር ረገድ የጎላ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣናው አገራት መካከል ለሚተገበረው ነፃ የንግድ ቀጣና መቀላጠፍ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም አየር መንገዱ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ባንጉይ በሳምንት ሶስት ጊዜ በረራ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የማዕከላዊ አፍሪካ አምባሳደር ፈርናንድ ኮኖ ተገኝተዋል።