ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሴራሊዮን ጋር ዛሬ ትጫወታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሴራሊዮን ጋር ዛሬ ትጫወታለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከሴራሊዮን ጋር ዛሬ ታደርጋለች።
የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በሞሮኮ ኤል ጃዲዳ ከተማ በሚገኘውና 15 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ኤል አብዲ ስታዲየም ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ እ.አ.አ በ2026 በአሜሪካ ፣ ካናዳና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት ይከናወናል።
በዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያን 54 አገራት በዘጠኝ ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ሴራሊዮንና ጅቡቲ ጋር ተደልድላለች።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው ገብረመድሕን ኃይሌ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞን ዛሬ ከሴራሊዮን ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል።
አሰልጣኝ ገብረመድሕን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅት ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ከጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅቱን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አሰልጣኙ በመጀመሪያ ዙር ጥሪ ካደረጉላቸው ተጫዋቾች መካከል ሰባቱን በመቀነስ የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን ይዘው ወደ ሞሮኮ አቅንተዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በሞላይ ረሺድ-ሲዲ ስታዲየም ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በ49ኝ ዓመቱ የሴራሊዮን የቀድሞ የፊት መስመር ተሰላፊ አሚዱ ካሪም የሚሰለጥነው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን 24 ተጫዋቾችን በመያዝ ለጨዋታው ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ስታሸንፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የ34 ዓመቱ ሞዛምቢካዊ አልቫካኦ ሴልሶ የሁለቱን አገራት ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ አንድ ግብጽ ከጅቡቲ ነገ እንዲሁም ቡርኪናፋሶ ከጊኒ ቢሳው ከነገ በስቲያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ሕዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም ከቡርኪናፋሶ ጋር ሞሮኮ ላይ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 አገራት የሚሳተፉ ሲሆን አፍሪካ ዘጠኝ አገራትን የማሳተፍ ኮታ ተሰጥቶታል።
በማጣሪያው ከየምድቡ አንደኛ የሚወጣ አገር በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫው የሚያልፍ ሲሆን ከዘጠኙ ምድቦች ምርጥ ሁለተኛ የሆኑ አገራት ወደ ሁለተኛው ዙር ያልፋሉ።
በሁለተኛው ዙር ሶስት ጨዋታ የሚደረግ ሲሆን በእርስ በእርስ ጨዋታው አሸናፊ የሆነ አገር ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ በሌላ አህጉር ከሚገኝ አገር ጋር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል።
በዚህም አፍሪካዊ አገር የጥሎ ማለፍ ጨዋታውን ካሸነፈ አህጉሪቷን ወክሎ በዓለም ዋንጫው የሚሳተፍ 10ኛ አገር ይሆናል ማለት ነው።