ቀጥታ፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ዒሳ አል ማዙሪ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ዒሳ አል ማዙሪ ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ በ18ኛው የዱባይ የአየር ትርዒት እና ኤግዚቢሽን ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።

በጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ከህዳር 3 እስከ 7/2016 ድረስ በሚካሄደው የዱባይ የአየር ትርዒት እና ኤግዚብሽን ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡

ዛሬ ህዳር 4/2016 ዓ.ም ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ዒሳ አል ማዙሪ ጋር በሁለቱ እህትማማች አገራት መካከል ስላለው ወታደራዊ ጉዳዮች ትብብር ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተሳትፏቸው ዓለማችን የደረሰችበትን አዳዲስ የአየር ቴክኖሎጂዎች መጎብኘታቸውም ተመላክቷል።


 

ከኤግዚብሽኑ ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት ወታደራዊ መሳሪያ አምራች ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እየተወያዩ መሆኑን በዱባይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር የኢፌዲሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በኤይር ሾዉ ላይ ተሳትፈዋል።

ከጉብኝቱ ጎን ለጎንም በኤይሮ ስፔስ ዘርፍ የካበተ ልምድ ያላቸው ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችን ማነጋገራቸውም ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜና የተለያዩ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የዱባይ አየር ትርዒት እና ኤግዚቢሽን ዘመናዊ የአየር ቴክኖሎጂዎች ለዕይታና ለገበያ የሚቀርቡበት ነው፡፡

ኤግዚቢሽኑ ዓለም አቀፍ የአየር ቴክኖሎጂ ትብብርን ለማበረታታት ከዓለም ዙሪያ ላሉ የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ የመከላከያ አባለት እና የኢንዱስትሪ መሪዎች እንደ ዋና መድረክ ሆኖ የሚያገለግል ኩነት መሆኑም በመረጃው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም