ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል በሚካሄደው የአገራዊ ምክክር ተሳታፊ ልይታ ላይ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ተጠየቀ

ጂግጂጋ፤ ህዳር 04/2016(ኢዜአ)፡-በሶማሌ ክልል በቀጣይ በሚካሄደው የአገራዊ ምክክር ተሳታፊ ልይታ ላይ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል በሚካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ ላይ የሚሳተፉ ተባባሪ አካላት የስልጠና መድረክ ዛሬ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መስጠት ጀምረዋል። 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ዲሪር የስልጠና መድረኩ ያስፈለገው ተባባሪ አካላት በኮሚሽኑ ተግባር እና ኃላፊነት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ነው ብለዋል። 

የዚህ ስልጠና ተሳታፊዎችም በሶማሌ ክልል11 ዞኖች፣ 96 ወረዳዎችና 6 ከተማ አስተዳደሮች በሚካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ ላይ ይሳተፋሉ ነው ያሉት።

ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉ ተባባሪ  አካለት ወደየ ወረዳዎቹ ሲመለሱ ግልፅ፣ ፍትሀዊ፤ አሳታፊና አካታች በሆነ ሁኔታ እያንዳንዱ ተባባሪ አካላት 10 ተሳታፊዎች ልየታ እንደሚያካሄዱ ተናግረዋል። 

ኮሚሽነሩ በክልሉ በቀጣይ ለሚካሄዱ ተግባራት ስኬታማነት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋፆ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።


 

የተባባሪ አካላት ስልጠናው ከህዳር 4 እስከ ህዳር 6 የሚቆይ ሲሆን በሀገራዊ ምክክር መድረክ አስፈላጊነት፣ የተባባሪ አካላት ኃላፊነት  እና ሀገራዊ ምክክር መድረክ አለም አቀፍ ተሞክሮ ላይ ያተኮረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከህዳር 11 እስከ 13 ተመሳሳይ ስልጠና በክልሉ ጎዴ ከተማ እንደሚካሄድ የተጠቀሰ ሲሆን ስልጠናው ከዚህ ቀደም የአቅም ግንባታ ስልጠና በወሰዱ የቀብሪዳሀር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ይሰጣል።

በስልጠናው ከክልሉ ምሁራን መድረክ አባላት፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያየ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 824 ሰዎች እየተሳተፉ ነው። 

ኮሚሽኑ እስካሁን በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች ከ5 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን መምረጡንም አስታውሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም