የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቢዝነስ ሕግን መሠረት ያደረገ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነትን የተከተለ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቢዝነስ ሕግን መሠረት ያደረገ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነትን የተከተለ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቢዝነስ ሕግን መሠረት ያደረገ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነትን የተከተለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።
ኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደብ የማግኘት ጥያቄ ማንሳቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ሀገራትና መላው ዓለም የኢትዮጵያን እውነተኛ ችግሮችና ፍላጎት መረዳት አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በፊት የሁለት ወደብ ባለቤት እንደነበረች አስታውሰዋል።
በወቅቱ የነበራት የሕዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚያዊ እድገት አነስተኛ እንደነበር በማስረዳት፤ ዛሬ ላይ የሕዝብ ቁጥሯና ኢኮኖሚዋ በብዙ እጥፍ ቢያድግም አማራጭ ወደብ የላትም ብለዋል።
የአካባቢው ጂኦ-ፖለቲካ ተለዋዋጭነትና ብልሽት ለኢትዮጵያ ስጋት በመሆኑ አማራጭ ወደብ ያስፈልጋታል ነው ያሉት።
የጂቡቲ መንግሥትና ሕዝብ ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ወደባቸውን እንድንጠቀም በማድረግ ላሳዩት አጋርነት አመስግነው፤ የባህር በርና የወደብ ተጠቃሚነትን በሚመለከት ያቀረብነውን ጥያቄ ጎረቤት ሀገራት በቀዳሚነት መረዳት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ያንን የሚሸከም አማራጭ ወደብ ማግኘት አስፈላጊ እንደሆነም አብራርተዋል።
በዓለም ላይ ቀይ ባህርን የማይፈልግ አገር እንደሌለ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ስለ ቀይ ባህር ተጠቃሚነት ስታነሳ ትክክል የማይሆንበት ምክንያት የለም ነው ያሉት።
የቀይ ባህርን ጉዳይ የኤርትራን ሉዓላዊነት ከመዳፈር ጋር አያይዘው የሚያነሱ አካላት ትክክል አለመሆናቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የማንንም አገር ሉዓላዊነት የመድፈር ፍላጎት የላትም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቢዝነስ ሕግን መሠረት ያደረገና በሰላማዊ መልኩ ምላሽን የሚሻ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ጎረቤት ሀገራት ለንግግር ሊዘጋጁ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ወደየትኛውም የጎረቤት ሀገር ጥይት የመተኮስም ሆነ ሉዓላዊነትን የመዳፈር ፍላጎት ፈጽሞ እንደሌላትም አረጋግጠዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወይም ሌሎች ድርጅቶች በማጋራት የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ማቅረባችንና ለጋራ እድገት ቁርጠኛ መሆናችንን ጎረቤት ሀገራትም ሆኑ የዓለም መንግሥታት ሊገነዘቡት ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት የሚነሳ የጦርነት ስጋት የለባትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሉዓላዊነቷን ለማስከበርና ለቀጣናው ሰላም አሁንም አበክራ ትሰራለች ብለዋል።
የኢትዮጵያን ፍትሃዊና ተገቢ የባህር በር ጥያቄ ላልተገባ ዓላማ አንሻፈው የሚያነሱ አካላትም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ነው ያሉት።