የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሁሉም አገራት ጋር ተስማምቶና ተጋግዞ ማደግ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሁሉም አገራት ጋር ተስማምቶና ተጋግዞ ማደግ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የምትፈልገው ከሁሉም አገራት ጋር ተስማማቶና ተጋግዞ ማደግን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።
6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሄዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 28/2016 ለሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና መስፈሪያ ሚዛን የአገር ውስጥ ፍላጎት ከሌሎች ጋር በሚኖር ትብብር የሚፈጸምና አብዛኛው የፖሊሲ መነሻ ከዚሁ የሚመነጭ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ፖሊሲው ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት እንዲሁም መልክዓ ምድራዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶችን መነሻ በማድረግ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሰጠና ወደፊት የሚፈጠረውን ቀጣናዊ ትስስር ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።
ከዚህም አንጻር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣናዊ ትስስርን እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ አንድ ወገን የመደገፍና ሌላውን የመቃወም አካሄድ ሳይሆን በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማት በመቀላቀል ድምጿን የማሰማትና ጥቅሟን የማስከበር የብዝሃ ወገን ዲፕሎማሲ ሥራ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎትና መሻት ከሁሉም አገራት ጋር ተስማምቶና ተጋግዞ ማደግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ የትኩረት አቅጣጫም ሁሉን አቀፍ አካሄድን የተከተለ መሆኑን አንስተዋል።