ባለፉት ሦስት ወራት 100 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ሦስት ወራት 100 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦ ባለፉት ሦስት ወራት 100 ቢሊየን ብር ተገኝቷል፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ12 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ገቢ እያደገ ቢሆንም ካለው አቅም አንጻር የተሻለ ገቢ ለማግኘት የተጠናከረ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት 407 ቢሊየን ብር ገቢ የተገኘ መሆኑን ጠቁመው በተያዘው በጀት ዓመት 520 ቢሊየን ብር ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 100 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ12 በመቶ እድገት ማሳየቱን ነው ያስረዱት።
ይህም አገሪቱ ከምታመርተው ምርት አንጻር አነስተኛ መሆኑን ተናግረው ይህንን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆን ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት 141 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ እድገት እንዳለው ጠቁመዋል።