የብሔር፣ ብሔረሰቦች በዓል ብዝኃነትን ዕውቅና የሚሰጥ፣ አንድነትን የሚያጠናክርና ሰላምን የሚያጸና ነው- አቶ አገኘሁ ተሻገር 

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦  የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ብዝኃነትን ዕውቅና ለመስጠት፣ እኩልነትን ለማስተናገድ፣ አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ። 

የፌደሬሽን ምክር ቤት ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል አከባበር የመሪ ሃሳብ ትንተና አስመልክቶ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። 


 

በመድረኩም የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ላለፉት 17 ዓመታት ሲከበር የቆየው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክብረ በዓል የሕዝቦችን አብሮነትና አንድነት በማጎልበት የርስ በርስ ትውውቅና የባህል ልውውጥ መድረክ ሆኖ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ገንቢ ሚና መወጣቱን ገልጸዋል። 

በዓሉ በሚከበርባቸው ክልሎች መሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት በማነቃቃት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍፃሜ ለማድረስ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል። 

18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ይከበራል ብለዋል፡፡ 

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን በፍትሐዊነት የተመሰረተ አገራዊ አንድነትን በመፍጠር ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ እንዲሸጋገር የማድረግ አደራ ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል። 

በዓሉ ብዝኃነትን ዕውቅና ለመስጠት፣ እኩልነትን ለማስተናገድ፣ አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት፣ በሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ሥርዓቱን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተው ለዚህም በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። 

የዘንድሮው በዓል ሲከበር የሕዝቦችን አንድነትና ትስስር በማረጋገጥ የአገር ሰላምና አንድነት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት የሚሰራበት መሆኑንም አፈ ጉባኤው አንስተዋል። 

በ18ኛው በዓል ላይ ብዝኀነትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በማጠናከር ኢትዮጵያ በሁሉም አውዶች አሸናፊ እንድትሆን ከመበታተን መሰባሰብ፣ ከመገፋፋት መደጋገፍ፣ ከግትርነት ይልቅ ለሐሳብ ልዕልና ቅድሚያ መስጠትና በወል ሁነቶች ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል። 

የመገናኛ ብዙኃንም የኢትዮጵያዊያንን አብሮነትና ብዝኅነት ታሳቢ በማድረግ ሕብረ-ብሔራዊ ትስስር እንዲዳብር ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። 


 

የመንግስታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የህገ-መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸኃፊ ባንቺይርጋ መለሰ፤ የኢትዮጵያን ብዝኅነት እና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር በዓሉ ወቅታዊ አገራዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ አድርጎ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። 

ሕብረ ብሔራዊነትን በማስጠበቅ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አብሮነት አጠናክሮ በማስቀጠል አገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል በፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት "ብዝኅነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ሚያዚያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም በ3ኛ የፓርላማ ዘመን በ1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ በ2ኛ መደበኛ ስብሰባ በየዓመቱ እንዲከበር ምክር ቤቱ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም