ቀጥታ፡

የዋጋ ግሽበቱ አምና ከነበረበት 37 በመቶ ዘንድሮ መስከረም ወር ላይ ወደ 28 በመቶ ወርዷል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦ የዋጋ ግሽበቱ አምና ከነበረበት 37 በመቶ ዘንድሮ መስከረም ወር ላይ ወደ 28 በመቶ መውረዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋጋ ግሽበትንና ሌብነትን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የዋጋ ግሽበት የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ችግር መሆኑን ጠቅሰው ዋጋ ግሽበቱ አምና 37 በመቶ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ መስከረም ወር ላይ ወደ 28 በመቶ ወርዷል ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመት እና በሚቀጥለው ዓመት የበለጠ ይወርዳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ በርካታ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ድጎማና ለአቅመ ደካማ ዜጎች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው የእሁድ ገበያ ማዕከላትን ማስፋፋትም የዚሁ ስራ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በከተሞች ያለውን የቤት ኪራይ ሁኔታ በህግ ለመግራት ይሰራል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌብነትን በሚመለከት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄም ሲመልሱ ሌብነት ተቋም የሚያፈርስ ምስጥ ነው ብለውታል፡፡

ውስብስብ ችግር በመሆኑም ብርቱ ትግል እንደሚጠይቅም በማመላከት፡፡

ሌብነትን የሚጸየፍ ባህልን ከመገንባት ባሻገር ከሰው እጅ ንክኪ ነጻ የሆነ ዲጂታል አሰራርን ማስፋት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ ገቢ መሰብሰብን ጨምሮ 190 የሚሆኑ አገልግሎቶችን ዲጂታል ማድረግ ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን ሌብነትን የመታገሉ ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም