ቀጥታ፡

ባንኮች ለብድር ካቀረቡት 547 ቢሊዮን ብር ውስጥ 86 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የቀረበ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦ ባንኮች ለብድር ካቀረቡት 547 ቢሊዮን ብር ውስጥ 86 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የቀረበ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የባንኮች የብድር አቅርቦትን፣ የእዳ ጫናን፣ የውጭ ምንዛሬን፣ ግብርናንና የኢንዱስትሪ እደገትን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በአጠቃላይ ባንኮች ለብድር ካቀረቡት 547 ቢሊዮን ብር ውስጥ 86 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የቀረበ ነው ብለዋል፡፡

ለግሉ ዘርፍ ከቀረበው ብድር ውስጥ አርሶ አደሩ 15 በመቶ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው ከዚህ ቀደም ከፍተኛውን ብድር የሚወስደው መንግስት የነበረ ሲሆን ይህንን ትርጉም ባለው መልኩ መቀየር መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡

የእዳ ጫናን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም ኢትዮጵያ የአገር ውስጥን ጨምሮ ያለባት እዳ አሁን ላይ 31 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

ከዚህም ወስጥ የውጭ እዳችንን ወደ 14 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ሲሉም አክለው በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታትም ከ10 በመቶ በታች ዝቅ ለማድረግ እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 23 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አግኝተናል ብለዋል።

ከዚህም ውስጥ ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን ከአገልግሎት ዘርፍ የተገኘ መሆኑን ጠቅሰው ይህን ወደ 25 ቢሊዮን ለማድረስ እየሰራን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ግብርናን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም እንዲሁ በዓመቱ ግብርናው የ6 ነጥብ 3 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ የሰብል ምርት 7 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ዘርፉም እንዲሁ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ከመጀመራችን በፊት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 47 በመቶ የነበረ ሲሆን በንቅናቄው አማካኝነት በአጭር ጊዜ ወደ 55 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ታምርት ላይ የታየው አፈጻጸም ተስፋ ሰጪ ስራ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም