የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ ከ10 በመቶ በታች ለማድረስ እየተሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ ከ10 በመቶ በታች ለማድረስ እየተሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ ጫና ከ10 በመቶ በታች ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፤ በተለይም የዕዳ ቅነሳን በተመለከተ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ዕዳ ቅነሳ ላይ ያተኮሩ ውጤታማ ስራዎችን መስራቷን ተናግረዋል።
ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው መንግስት በተከታታይ ዓመታት ዕዳ ቅነሳ ላይ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ ዕዳ በአንጻራዊነት የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት አጠቃላይ ዕዳ በአማካይ 55 በመቶ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነዚህ አገራት አማካይ የውጭ ዕዳ 25 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዕዳ 31 በመቶ መሆኑን ገልጸው የአገሪቷ የውጭ ዕዳ 14 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ውጤት ማስመዝገብ የተቻለው አገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ባለችበት ወቅት መሆኑ ደግሞ መንግስት ለጉዳዩ የሰጠውን ትልቅ ትኩረት ያሳያል ብለዋል።
በጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ ጫና ወደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመንግስትን የአገር ውስጥ ዕዳ ለማቃለል የብድር ምጣኔን ከመቀነስ ጀምሮ በተሰሩ ስራዎች ውጤት መመዝገቡንም ጠቁመዋል።