በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው- ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው- ቢሮው
ሐረር፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የጤና ቢሮው ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ ኮሌራ በሽታ የተከሰተው ከሐምሌ 27 ቀን 2015 ጀምሮ ነው።
በሽታውን ለመከላከልም በቢሮ ደረጃ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሽታውን ለመቆጣጠር የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም፣ የድንገተኛ ሕክምና ግብዓቶች የማሟላት ሥራዎችን እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ አራት ጊዜያዊ የኮሌራ የሕክምና ማዕከላት ተዘጋጅተው በበሽታው ለተያዙ ሰዎች ሕክምና መሰጠቱን ኃላፊው አመልክተዋል።
በክልሉ አራት ወረዳዎች በተከሰተው በሽታ እስካሁን ድረስ 50 ሰዎች መያዛቸውን በምርመራ መረጋገጡን ገልጸዋል።
በበሽታው ከተያዙት መካከልም 48ቱ ታክመው መዳናቸውንና አንድ ሰው በለይቶ ማቆያ ህክምና እየተከታተለ መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው፣ በበሽታው አንድ ሰው ማለፉን ተናግረዋል።
በሽታውን ለመቆጣጠር የጉድጓድ ውሃን የማከም፣ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥና በጤና ተቋማት የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ የአካባቢ ንጽህናን እንዲጠብቅና ውሃን አክሞ እንዲጠቀም ያስገነዘቡት አቶ ያሲን፣ የበሽታው ምልክቶችን ሲመለከት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የሕክምና አገልግሎት እንዲከታተል አሳስበዋል።