የኦዲት ግኝቶችን በማያስተካክሉ ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የበኩላችንን እየተወጣን ነው- አፈ ጉባኤዎችና ቋሚ ኮሚቴዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኦዲት ግኝቶችን በማያስተካክሉ ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የበኩላችንን እየተወጣን ነው- አፈ ጉባኤዎችና ቋሚ ኮሚቴዎች
ሀዋሳ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) የኦዲት ግኝቶች እንዲታረሙ ከማድረግ ባለፈ የሚሰጣቸውን አስተያየት በማካተት በማያርሙ ተቋማት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ እየሰሩ መሆኑን አፈ-ጉባኤዎችና ቋሚ ኮሚቴዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እንደተናገሩት የኦዲት ግኝቶችን በማስመለስ የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል እየሰሩ ነው።
የኦዲት ግኝቶች እንዲታረሙ ከማድረግ ባለፈ የሚሰጣቸውን አስተያየት በማካተት በማያርሙ ተቋማት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ሂደት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፀሐይ ደረጃ እንዳሉት ለልማት የሚመደብ የመንግስት በጀት ከብክነት በፀዳ መልኩ ሥራ ላይ መዋል አለበት ።
ምክር ቤቱ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ በኦዲት ሪፖርቶች የሚቀርቡ የኦዲት ግኝቶች እንዲመለሱ በማያደርጉ ተቋማት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ኃይል ሰብሳቢ መሆናቸውን ያነሱት ወይዘሮ ፀሐይ የኦዲት ግኝቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ረገድ በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች የግልፀኝነትና ተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን እየተደረገ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቶች የህዝብ ውክልና እንደመያቸዛው መጠን አስፈጻሚ ተቋማት የተመደበላቸውን ሃብት በአግባቡ ስለመጠቀማቸው የመከታተል ሃላፊነት እንዳለባቸውና የተጠያቂነት ስርዓትን በበላይነት መምራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ክልል ምክር ቤት የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሉቅማን አብዱልቃድር በበኩላቸው ተገቢውን አሰራር ባለመከተል የሕዝብን ተጠቃሚነት በሚጎዱ ተቋማት ላይ የሚፈጠሩ የኦዲት ግኝቶች እንዲመለሱና እርምጃ እንዲወሰድባቸው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ክልል እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ሲንከባበል የመጣ 59 ሚሊዮን ብር የኦዲት ግኝት ለማስመለስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም ውስጥም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከአራት ሚሊየን ብር በላይ ማስመለሳቸውን ገልጸዋል።
የኦዲት ግኝትን ባላስተካከሉ 5 ተቋማት ላይም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለሚመለከተው አካል ማስተላለፋቸውን ገልፀዋል።
እንደ ሃገር ያለውን ውስን ሃብት በመጠቀም የሕዝብ ዘላቂ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ህግ-አውጪው፣ አስፈፃሚውና ተርጓሚው በቅንጅት መስራት አለባቸው ያሉት ሰብሳቢዋ ለዚህም ምክር ቤቶች የመሪነት ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ከሪማ አሊ በበኩላቸው፤ ኦዲት ተደራጊ ተቋማት የሚገኙባቸውን የኦዲት ግኝቶችን እንዲያስተካክሉ በማድረግና እርምት በማያደርጉት ላይ ደግሞ እርምጃ እንዲወሰድ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ምክር ቤት ከሚሰራው ሥራ ባለፈ ከኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ኃይል ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ ያለው ጅምር እንቅስቃሴ የግልፀኝነትና የተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ሰለመሆኑም ተናግረዋል።
በዘርፉ ውጤታማ ተግባር እያከናወኑ ካሉ ክልሎች ያገኙትን ተሞክሮ በመቀመር የህዝብና የመንግስት ሃብት ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲውል በማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን እንደሚያጠናክሩ ጠቅሰዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት የመረጣቸውን ሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስ የሚያስችል በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በሃቀኝነት መሥራትና ምሳሌ መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል።
የሕዝብና መንግስትን ሃብት በሚያባክኑ ተቋማትና አመራሮች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ትግል በማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱም ገልፀዋል።
22ኛው የዋና ኦዲተሮችና የባለድርሻ አካላት ጉባኤ ላለፉት ሶስት ቀናት በሀዋሳ መካሄዱ ይታወሳል።