ቀጥታ፡

መንግሥት ለበርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለበርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ ስብሰባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 28/2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር መሰረት በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ብልጽግና ፓርቲ መራሹ መንግሥት ለበርካታ ጥያቄዎች ጥናትን መሰረት ያደረጉ ድፍረት የተሞላባቸው ምላሾች መስጠቱን ተናግረዋል። 

ለአብነትም ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ መንግሥትና አገር እየመራ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ ትልልቅ ውሳኔዎች መወሰናቸውን ጠቁመዋል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ መንግሥታቸው በሰራው ጠንካራ ሥራ ብዙ ነገሮች መሻሻላቸውን ተናግረዋል። 

ከዚህም ባሻገር በኢኮኖሚው ዘርፍም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው በግብርናና በፕሮጀክቶች አፈጻጸም የተገኙ ውጤቶች ከፍተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።  


 

በፖለቲካው ረገድም በደቡብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ይነሱ ለነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎች የተሰጠውን ፖለቲካዊ ምላሽ ለአብነት አንስተዋል። 

የተቃዋሚ አባላትን የካቢኔ አባል በማድረግ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ መሞከሩንም አስረድተዋል። 

እነዚህ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ በመሆኑ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በአማራና ትግራይ ክልሎች ከወሰን ጋር በተያያዘ ለሚነሱ አጨቃጫቂ ጉዳዮችም መንግሥት ምላሽ እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል። 

መንግሥት የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጥ ሕዝበ ውሳኔን መሰረት ያደረገ አካሄድ ብንከተል ይሻላል ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል። 

ይህ ብቸኛ መፍትሄ ላይሆን ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሻለ አማራጭ ካለ ይምጣና ውይይት ይደረግበት ብለዋል። 

ነገር ግን ምንም አይነት መፍትሄ ሳያመነጩ ሁሉንም ነገር በደፈናው መቃወም አግባብ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል። 

በሁሉም መስክ ጥያቄዎች የሚቀጥሉ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትና ፓርቲያቸው ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም