ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልሉን መንግሥት ከመፍረስ አደጋ ታድጓል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦  በአማራ ክልል የታወጀው  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልሉን መንግሥት ከመፍረስ አደጋ መታደጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። 

በማብራሪያቸውም በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዋነኛው ዓላማው ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ነው ብለዋል።  

በጉልበት የክልል መንግሥት እናፈርሳለን ብለው የተነሱ ኃይሎች እንደነበሩ ጠቁመው፤ የክልሉ መንግሥት ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የፌደራል መንግሥት ገብቶ እንዲያግዝ ባቀረበው ጥያቄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተናግረዋል።  

በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁም አንጻራዊ ሰላም መረጋገጡን ጠቁመዋል። 

አዋጁ የክልሉን መንግሥት ከመፍረስ አደጋ ታድጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሟላ ሠላም ለማምጣት ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል። 

አሁን ላይ የነበረው ሥጋት መቀልበሱን ጠቁመው፤ የተሟላ ሰላም እንዲመጣ ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልግም አክለዋል። 

"የኢትዮጵያ ሕዝብ ብልጽግና ፓርቲን አምኖ መምረጡ ትክክለኛ ምርጫ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠራ ኃሳብና ተግባር ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በከፍተኛ ትጋት እንሰራለንም ሲሉም አረጋግጠዋል።

የሕዝቡ ጥያቄ የሆኑትን እንደ ሰላም፣ ሁሉም ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ መሻት እንደሚያስፈልግና ለማሳካትም እንሰራለን ብለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም