አስራ ሰባት ኩባንያዎችን ያቀፈ የቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ፌዴሬሽን ልዑክ አዲስ አበባ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
አስራ ሰባት ኩባንያዎችን ያቀፈ የቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ፌዴሬሽን ልዑክ አዲስ አበባ ገባ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2016 (ኢዜአ) ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ያደረጉትን የቻይና ጉዞ ተከትሎ አስራ ሰባት የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቻይና የነበራቸው ጉብኝት የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል 14 ሥምምነቶች መፈረማቸው ይታወሳል።
ከዚህም ውስጥ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር የሚረዳ ሥምምነት ተፈራርመዋል።
ይህንንም ተከትሎ በቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ፌዴሬሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ዙ ሌጀንግ የተመራ አምስት የልዑካን ቡድን ያካተተ 17 ኩባንያዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።
ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ በብረታ ብረት፣ በግብርናና በማዳበሪያ ምርትና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች ላይ ማዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎችና ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በተገኙበት ለኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ገለጻ ተደርጓል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
የኢንቨስትመንት መድረኮችን የአገራቱን ግንኙነቱ ብቻ ሳይሆን ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገውን የኢንቨስትመንት ፍሰት የበለጠ ለማጠናከር አስዋጽዖ ያደርጋልም ነው ያሉት።
የቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ፌዴሬሽን በስሩ 4 ነጥብ 7 ሚሊየን አባላት እንዳሉት ተገልጿል።