የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የፊታችን ኅዳር 8 በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የፊታችን ኅዳር 8 በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፣ህዳር 4/2016(ኢዜአ)-የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የፊታችን ኅዳር 8 በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ እንደሚከናወን ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኢትዮጵያን በመወከል ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።
ፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫውን አስመልክቶ ትናንት ማምሻውን ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቀደም ሲል በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ እንደሚከናወን የተገለፀ ቢሆንም፤ በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ወደ አዲስ አበባ ተዛውሯል።
ይህም የሆነበት በዕጩዎች ተገቢነት ላይ የተነሳውን ጥያቄ ከመረመረና ኢትዮጵያ ያቀረበችው ዕጩ ላይ ምንም አይነት ጥያቄ ባለመነሳቱ ምርጫው አዲስ አበባ እንዲካሄድ ተወስኗል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት እያሱ ወሰን ምርጫውን ካሸነፉ ለኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት መልካም ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ምርጫውንም ካሸነፉ የቦክስ ማዘውተሪያ ቦታዎች እንዲሰሩ፣ ሀገራዊና አህጉራዊ የቦክስ ውድድሮች በስፋት እንዲከናወንና የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ ያደርጋል ሲሉም አክለዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ምርጫው የኢትዮጵያን የቦክስ ስፖርት ገጽታ ለመቀየር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ለምርጫው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አመላክተዋል።
በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከአቶ እያሱ በተጨማሪ ከካሜሩን በርትራንድ ሜንዱጋ እና ሞሮኮዊው መሐመድ ኤል ካቡሪ ይወዳደራሉ።
የኮንፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አዛንዚያ ኦሞ-አጌጌ ከናይጄሪያና የዩጋንዳ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሞሰስ ሙሃንጊ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸውን የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መረጃ አመላክቷል።
ከቀረቡት ዕጩዎች የተሻለ ድምጽ ያገኘው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በመሆን ለአራት ዓመት ፌዴሬሽኑን ይመራል።