ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ቅነሳ መርሐ ግብሯ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖን ለመቀነስ እያደረገች ባለው ጥረት የሴቶችን የመሪነት ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዩኔስኮ እና በኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ኤምባሲ ጋር የሴቶች ተሳትፎ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያለውን ሚና በተመለከተ ውይይት አካሂደዋል፡፡


 

የአየር ንብረት ለውጥ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ለድህነትና ለችግር ከተጋለጠው የዓለም ህዝብ መካከል 60 በመቶ ሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ በተፅዕኖው ከሚፈናቀሉ መካከል 80 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያሳያል።

አፍሪካ ወደ ከባቢ አየር የምትለቀው የበካይ ጋዝ መጠን ዝቅተኛ ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርስባት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከሁሉም የላቀ ነው፡፡

እንደ አህጉር 70 በመቶ የሚሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚስተናገደው በግብርናው ዘርፍ ላይ ሲሆን ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገሮች ደግሞ የከፋ እንደሆነ ይገለፃል፡፡

በዚሁ ቀጣና ባሉ ሀገራት ከሚኖሩ ሴቶች 60 በመቶዎቹ በአየር ንብረት ለውጥ እየተጎዳ በሚገኘው የግብርናው ዘርፍ የሚሰሩ ሲሆን 70 በመቶውን የምግብ ፍጆታ የማምረት ጫናን የተሸከሙ ናቸው።

የአየር ንብረት ለውጥም በእነዚሁ ሴቶች ላይ የከፋ ጫና እያሳደረ መሆኑ ይነገራል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሴቶች ሚና የጎላ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ስትተክል ሴቶች አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣትና በዓለም ነባራዊ ሁኔታ ላይ ለውጥ ለማምጣት ሴቶችን በሚገባ ማብቃት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በምታከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ላይ የሴቶችን ሚናና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የጀመረችውን ስራ አጠናከራ እንደምትቀጥል ጠቁመዋል፡፡


 

በኢትዮጵያና አፍሪካ ህብረት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ተወካይ ሳኦድ አል ታኒጂ፤ ሀገራቸው በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ፕሮጀክት ላይ የሴቶችን ሚና ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሴቶች በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም፤ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና መሰል ዘርፎች ላይ የላቀ ሚና እንዲኖራቸው እድል ትሰጣለች ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሱናት በዓለም ላይ ደረጃው ይለያይ እንጂ ሴቶች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ለሴቶች የሚሰጣቸው ውክልና ዝቅተኛ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በመሆኑም የሴቶችን አካታችነት፣ ውሳኔ ሰጭነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ማከናወን የግድ ነው ብለዋል፡፡

ዩኔስኮ የሴቶችን የመሪነትና ውሳኔ ሰጭነት ሚና ለማሳደግ ከመንግስትና ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በትብብር ለመስራት ሁልጊዜም ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም