በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል
አሶሳ ፤ ህዳር 3 / 2016(ኢዜአ) ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡
የመንገዶቹን ግንባታ ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አባላት ዛሬ በአሶሳ ተወያይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አማካሪ ኢንጂነር አበበ አሰፋ በወቅቱ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳብራሩት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳዳር ግንባታቸው ከተጀመሩት መካከል ሆሞሻ - ህዳሴ ግድብ፣ አይሲዲ - ኮንግ፣ አሶሳ - ዳለቲ - ባሩዳ፣ ያሶ - ጋሌሳ ዲባጤ፣ ያሶ - ዲባጤ - ጋሌሳ - ቻግኒ እና ካማሽ - ሶጌ ለቀምት ይገኙበታል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ተስተጓጉለው የቆዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ስራቸውን ለማስቀጠል ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሃመድ አብዱራህማን በወቅቱ፤ ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ በማስጀመርና ለውጤት ለማብቃት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መንገዶች በቅርቡ ለማስጀመር አስተዳደሩ አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቁመዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ጥናት ዲዛይን እና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ዮሴፍ በበኩላቸው፤ ክልሉ ካለው ከ2 ሺ 500 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ውስጥ 90 በመቶው የጠጠር መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚወስደውና ከባድ ተሸከርካሪዎች የሚያስተናግደው መንገድ ከ15 ዓመት በፊት የተገነባ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና በወቅቱ ባጋጠመ የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚገባ አለመፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡
አስተዳደሩ ችግሮቹን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለማስተካከል በአካል፣ በስልክ እና በሌሎችም አማራጮች ስራውን ክትትል በማድረግ የመንገድ ግንባታውን ለማስቀጠል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አድንቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የትኛውም ዞን ወረዳ እና ቀበሌ ውስጥ ልማት ለማከናወን የሚያስችል ሰላም መኖሩን አመልክተው፤ አሰራርን በመከተል መንገዱ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመቀናጀት ሲሚንቶ፣ ነዳጅ እና ሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት እንዲጠናከር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡