"አሸባሪው ሸኔ እየተወሰደበት ባለው ከባድ ምት የአጥቂነት መንፈሱ ተሰብሯል" - ሌተናል ጀነራል ዲሪባ መኮንን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2016(ኢዜአ)፦ "አሸባሪው ሸኔ እየተወሰደበት ባለው ከባድ ምት የአጥቂነት መንፈሱ ተሰብሯል" ሲሉ ሌተናል ጀነራል ዲሪባ መኮንን ገለጹ።

በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በቀጠናው የሚገኙ አምስት ዞኖች፣ የወረዳና ከተማ መስተዳድር የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የምዕራብ ዕዝ አመራሮች እና የክልሉ የፀጥታ አካላት በተገኙበት በአካባቢው ሠላምና ፀጥታ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡


 

በምዕራብ ወለጋ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው የሸኔ ቡድን መከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ የፀጥታ አካላት በቅንጅት እየወሰዱት ባለው ርምጃ ሃይሉ እየተዳከመ፣ ከህዝቡ እየተነጠለ እንዲሁም የሎጀስቲክስ አቅርቦቱ እየነጠፈ መምጣቱ ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የገጠር ልማት ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ ከአመት በፊት የአካባቢው ህብረተሰብ በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ ነበር ፤አሁን ግን ህዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል፤ ስራ አቁመው የነበሩት ትምህርት ቤቶች እና የጤና ኬላዎች ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም ያለምንም ስጋት ገበያ ወጥቶ ተገበያይቶ መግባት መጀመሩን ጠቅሰው፤ የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለዚህ ቀን ላበቁን የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ ስኬት ወደ ኋላ እንዳይመለስ በትጋት መስራት ከሁላችን ይጠበቃል ማለታቸውንም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌተናል ጀነራል ዲሪባ መኮንን በበኩላቸው ሸኔ እየተወሰደበት ባለው ከባድ ምት የአጥቂነት መንፈሱ ተሰብሯል፤ ከውጪም ከውስጥም ድጋፍ እያጣ በመምጣቱ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በመግባት ባገኘው አጋጣሚ እየሸሸና እየተደበቀ ነው ብለዋል።
 

የአካባቢው ህዝብም ሰልችቶኛልና የሸኔን ቀብር አፋጥኑልን ማለቱን ተናግረዋል፡፡


 

የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሰለ መሰረት ፤ በአሁን ወቅት የክልሉ የመንግስት መዋቅርና የአካባቢው ህብረተሰብ ለተልዕኳችን ስኬታማነት አጋዥ ሚና እየተጫወቱ በመሆናቸው ለግዳጃችን ውጤታማነት ትልቅ ፋይዳ አለው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ጠላት በአሁን ወቅት ህልውናውን ለማቆየት በዉሸት ፕሮፖጋንዳ ላይ ተጠምዷል ያሉት አዛዡ ህዝቡ የሰላምና የልማት ተቋዳሽ እንዲሆን የሸኔ አጀንዳ መዘጋት ስላለበት በአሸባሪዉ ሸኔ ላይ የሚወሰደዉ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም