የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል የተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎች ልየታ ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል የተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎች ልየታ ስራ ጀመረ
ጅግጂጋ ፤ ህዳር 3 / 2016(ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል የተባባሪ አካላት እና ተሳታፊዎች ልየታ ስራ ጀመረ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር መሀሙድ ዲሪር፤ በሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ሀገራዊ የምክክር መድረክ ወክሎ የሚሳተፉ አካላትን ለመለየት ስለ ሚያከናወናቸው ስራዎች አስመልክቶ ማምሻውን በጅግጅጋ ከተማ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚሁ መግለጫቸው፤ በሀገራዊ ምክክርን የሚሳተፉ የተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመምረጥ በሶማሌ ክልል ባሉ 11 ዞኖች ስር በሚገኙ 95 ወረዳዎችና ስድስት ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ 824 ተባባሪ አካላት ተለይተዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ መሰረታዊና የማንግባባቸው ጉዳዮች በጋራ በመምከር መፍትሄ ለማበጀት ታምኖበት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል ።
ኮሚሽኑ ለጀመራቸው ስራዎች ስኬታማነት በሶማሌ ክልል የተባባሪ አካላት እና የተሳታፊዎች ልየታ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል ።
በኮሚሽኑ የተለዩ ተባባሪ አካላት ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የመጀመሪያው ዙር ስልጠና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የስልጠናው ሁለተኛ ዙር በቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በኮሚሽኑ የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱ የዩኒቨርሲቲው መምህራን በጎዴ ከተማ በሶማልኛ ቋንቋ እንደሚከታተሉም ጠቅሰዋል።
ተባባሪ አካላቱ ከስልጠናው በኋላ ወደየአከባቢያቸው በመመለስ ከአስተዳደር አካላት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግሥት ሰራተኞች፣ከሀገር ሽማግሌዎች ፣ከአርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች፣ ከእድር አባላት፣ከአካል ጉዳተኞች፣ ከሴቶችና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካይ እንደሚመርጡ አስታውቀዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳመለከቱት፤ በየወረዳው የሚመረጡ አስር አስር ሰዎች ውስጥ ሁለት ሁለት በመምረጥ ክልሉን ወክሎ አጃንዳዎቻቸውን በመያዝ በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ ይደረጋል።
ሂደቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ፣በገለልተኝነትና በታማኝነት የሚከናወን በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ 5 ሺህ ግለሰቦችን የመለየት ስራን በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ማስመረጡንም አምባሳደር መሀመድ አስታውሰዋል።