በሲዳማ ክልል በተመረጡ የመንግስት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ሊተገበር ነው

191

ሀዋሳ፤ ህዳር 3 / 2016 (ኢዜአ) ፡-  በሲዳማ ክልል በተመረጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ለመተግበር  ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ዘመናዊና ቀልጣፋ የፋይናንስ አሰራር ለመዘርጋት  የሚያስችል  የውል ስምምነት  ዛሬ ከአንድ ድርጅት ጋር ተፈራርሟል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የቢሮው  ኃላፊ ዶክተር አራርሶ ገረመው እንዳሉት ፤ በክልሉ በተመረጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ይተገበራል።

በዚህም በክልሉ ከሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል በድህነት ቅነሳ መርሃ ግብር አተኩረው በሚሰሩ ስድስት ቢሮዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር ከነገ ጀምሮ ለመተግበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የፋይናንስ፣  የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት፣ ውሃና ማዕድን፣መንገድና ትራንስፖርት ልማት፣ ገቢዎች ቢሮዎችና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ተግባራዊ ከሚደረግባቸው መካከል የጠቀሷቸው ናቸው።

ስርዓቱ የሚባክኑ ሀብቶች ለማዳን የሚያስችል ምቹ መደላድል መሆኑን አንስተው፤  የፋይናንስ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን በማስፈን  በህዝብና መንግስት መካከል መተማመን እንደሚያጎለብት አስረድተዋል።

በተለይም በመንግስት መስሪያ ቤቶች ከጨረታ ሂደት ጋር በተያያዘ ያለውን የወረቀት ንኪክና የጊዜና ጉልበት እንዲሁም አለአግባብ የሚወጡ የተለያዩ ወጪዎችን ማስቀረት የሚያስችል አሰራር መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈ ክልሉ የፋይናንስ ግልጸኝነትን ለማጠናከር ከ45 በላይ የመንግስት ተቋማት የ"ኦን ላይን " አሰራር በመዘርጋቱ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ቼክ አልባ አሰራር ለመዘርጋት ከባንኮች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከቢሮው ጋር ስምምነቱን የተፈራረመው ፔራጎ ኢንፎርሜሽን  ኃ.የተ.ግ.ማ. የተሰኘው የሶፋትዌር ድርጅት ሃላፊ አቶ እውነቱ አበራ፤  የዘመናዊና ቀልጣፋ የፋይናንስ አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን  ገልጸዋል።

ይህም በመንግስት ግዥ የሚወዳደሩ ተቋማት ያለቦታ ገደብ እኩል በሆነ አሰራር ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የፋይናንስ ህግ በአግባቡ እንዲተገበር፣የጊዜና ጉልበት ብክነት ከመቀነስ ባለፈ ከተለያዩ አማራጮች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ለጨረታና መሰል ግዥዎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚያስቀር መሆኑን አመላክተዋል።

የፌዴራል ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ በበኩላቸው፤  የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓትን መተግበር በፋይናንስ አሰራር ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ለማስወገድ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

እንዲሁም “ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን፣ ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ፣በመንግስትና በህዝብ መካከል መተማመን እንዲኖር ያደርጋል" ብለዋል።

እንደሀገር ዘርፉን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤  የሲዳማ ክልል መተግበሪያውን በመጠቀም የዘመነ የፋይናንስ አሰራር ለመከተል እንደተዘጋጀ መረዳታቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል ከሐምሌ 2015 ዓም ጀምሮ ለተመረጡ ቢሮዎች  ባለሙያዎች ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

እንደ ሀገር አሁን ላይ 163 ፌዴራል መስሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት መተግበር ጀምረው የታለመለት ውጤት እየተገኘ መሆኑን አንስተው፤  ወደ ሌሎች ክልሎች የማስፋት ስራ እንደሚቀጥል  ጠቁመዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም