የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስከበር የዜጎችና የተቋማት ጥረት ወሳኝ ነው-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስከበር የዜጎችና የተቋማት ጥረት ወሳኝ ነው-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 3/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስከበር የዜጎችና የተቋማት በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ጥረት ወሳኝ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ።
አገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የህብረተሰቡን ንቃት ህሊና ከፍ የሚያደርጉ ተግባራትን በማከናወን በስኬት መጠናቀቁንም አስታውቋል።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ከጥቅምት 1-30/2016 ዓ.ም " አይበገሬ የሳይበር አቅም ለሀገር ሉዓላዊነት " በሚል መሪ ሀሳብ የተከበረውን አገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወርን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ወሩ የህብረተሰቡን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ከፍ የሚያደርጉ ዝግጅቶች የቀረቡበት ነው ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ላይ የሚፈጠረው ንቃተ ህሊና ለአገር የሳይበር ደህንነት ተጨማሪ አቅም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በፋይናንስ፣ ቁልፍ መሰረተ ልማት፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑት ተቋማት ላይ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተቋማት የሳይበር ደህንነት ንቅናቄውን በመቀላቀል የመከላከል ዝግጁነታቸውን እንዲያሻሽሉ ማስቻሉን እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማነቃቃቱንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስከበር የዜጎችና የተቋማት በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ጥረት ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።
የሀገሪቱን የሳይበር ምህዳር በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቁ ወጣቶችን ከማፍራት አንጻር መነቃቃት መፈጠሩን ገልጸው፤ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በርካታ የምርምር ውጤቶች፣ ወቅታዊ መረጃዎች፣ የአፈጻጸም ሪፖርቶችና የግንዛቤ መልዕክቶችም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን፣ ቢልቦርድ፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ ዲጂታል ስክሪኖች እና ሌሎችም ዘዴዎች መልዕክቶቹ ተደራሽ ከተደረጉባቸው መካከል ናቸው ብለዋል፡፡
በሳይበር ደህንነት ወር ስውር ውጊያ የተሰኘ ፊልም መመረቁ፣ በርካታ ሰዎች የተገኙበት አውደ ርእይ መዘጋጀቱ እንዲሁም ግንዛቤን ከፍ የሚያደርጉ ውይይቶች መካሄዳቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጥቅሉ ስኬታማ ነበር ብለዋል።