በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስለሚኖር የደረሱ ሰብሎችን በአፋጣኝ መሰብሰብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስለሚኖር የደረሱ ሰብሎችን በአፋጣኝ መሰብሰብ ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 3/2016 (ኢዜአ) ፦ በመጪዎቹ አስር ቀናት በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስለሚኖር የደረሱ ሰብሎችን በአፋጣኝ መሰብሰብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ይህን ያለው በመጪዎቹ አስር ቀናት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረውን የአየር ፀባይ ሁኔታን በተመለከተ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ነው።
በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስተናግዱ የትንበያ መረጃው ያሳያል።
በተጨማሪም በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ በሚገኙ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ ከባድ ዝናብ እንደሚኖር አመላክቷል።
በኦሮሚያ ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ምዕራብ አርሲ ሁሉም የባሌና ጉጂ ዞኖች፣ ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ፣ የቦረና ዞን፣ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ የደቡብ ጎንደር፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ጠቁሟል።
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ የሲዳማ ክልል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የሶማሌ ክልል፣ ሀረሪ ክልልና ድሬዳዋም በተመሳሳይ።
ከላይ የተጠቀሱት አካባቢዎች በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ስለሚያገኙ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል።
በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል፣ መካከለኛው ኢትዮጵያ፣ የሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ምስራቅ ጎጃም፣ የማዕከላዊና የሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ የምዕራብና የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞኖች፣ ከአፋር ክልል ዞን 3፣ ዞን 5፣ ዞን 4 እና ዞን 1 ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖራቸው በትንበያው ገልጿል።
በበጋ ሁለተኛው የዝናብ ወቅትን የሚያስተናግዱ የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋለው እርጥበታማ የአየር ጸባይ ሁኔታ በደጋ አካባቢ ለተዘሩ ሰብሎች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስታውቋል።
በአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የእጽዋት ልምላሜን ለማሻሻል፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የውሀ ምንጮችን ለማጎልበት እና ለእንስሳት የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሀ አቅርቦትን ለማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመላክቷል።
በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው ርጥበታማ የአየር ሁኔታ ለጓሮ አትክልቶች፣ አርሶ አደሩ ለሚዘራቸው የጥራጥሬ ሰብሎች እና ወቅቱን ጠብቀው ላልተዘሩና እድገታቸው ገና ለሆኑ ሰብሎች በበቂ ሁኔታ ውሀ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚኖረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በአፋጣኝ መሰብሰብ እንደሚገባ አስጠንቅቋል።
በገናሌ ዳዋ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ኦሞ ጊቤ፣ መካከለኛውና ታችኛው ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛውና መካከለኛው ዓባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ የታችኛው ተከዜ ተፋሰሶች የሚኖረው ርጥበታማ የአየር ሁኔታ የውሃ ሀብትን ለማሻሻል አወንታዊ ሚና ቢኖረውም፤ የጎርፍ ተጋላጭነትን ሊያስከትል ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።