ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የተገነቡ ውብና አስደናቂ ፓርኮች ተመራጭ የመዝናኛ ሥፍራዎች ናቸው - የውጭ አገራት ጎብኚዎች

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 3/2016 (ኢዜአ) ፦ በአዲስ አበባ የተገነቡ ውብና አስደናቂ ፓርኮች የሚመቹና ተመራጭ የመዝናኛ ሥፍራዎች መሆናቸውን የተለያዩ አገራት ቱሪስቶች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአዲስ አበባ የተገነቡት የተለያዩ ፓርኮች የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻና የከተማዋ የውበት መገለጫ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።


 

ፓርኮቹ የሀገር ውስጥና የተለያዩ አገራት ቱሪስቶች መዳረሻ በመሆን ተመራጭ የመዝናኛ ሥፍራና የገቢ ምንጭም መሆን ችለዋል።

በእንጦጦ ፓርክ እና የወዳጅነት አደባባይ በጉብኝት ላይ ከነበሩት የውጭ ዜጎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ቱሪስቶች የፓርኮቹን ውበትና ለጉብኝት ያላቸውን ምቹነት አድንቀዋል።

እንጦጦ ፓርክን ሲጎበኙ ያገኘናቸው ናይጄሪያውያኑ ኦሞውኒ ኦሞሴያፋኒ እና ቴሜታዮ አጂሎሬ፤ ኢትዮጵያ ለቱሪስቶች ምቹ የሆነችና በርካታ ሊታዩ የሚገባቸው ኃብቶች ያሏት ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።


 

በአዲስ አበባ የእንጦጦ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች ውብና አስደናቂ ሥፍራዎች ደግሞ የከተማዋ ተጨማሪ ውበቶችና የጎብኝዎችን ቀልብ የሚገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በእንጦጦ ፓርክ ጉብኝታቸው በከፍታ ቦታ ላይ በነፋሻማው አየር እየተደሰቱና የአዲስ አበባን ውብ ገጽታ እየተመለከቱ ማሳለፋቸውን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ እያደረጉት ባለው ጉብኝት የአየር ንብረቱ ምቹነት፣ የመልክዓ-ምድሩ ውበት፣ የሕዝቡ እንግዳ አቀባበል በእጅጉ አስደስቶናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ቢታዩ የማይሰለቹ በርካታ ኃብቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ቱሪስቶቹ በአዲስ አበባ የአንድነት፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና ሌሎችም አካባቢዎች መጎብኘት ያለባቸው ልዩ ሥፍራዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከአሜሪካ ከባለቤቷ ሱራፌል ደረጀ ጋር ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው አፊያ ንኮላንሰን እንጦጦ ፓርክን ስለወደድኩት በቀናት ልዩነት ደጋግሜ እየመጣሁበት ነው ብላለች።


 

በአዲስ አበባ እንዲህ ዓይነት ፓርኮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለጎብኝዎች ክፍት በመደረጋቸው አድናቆቱን የገለጸው ደግሞ ሱራፌል ደረጀ ነው።

በአንድነት ፓርክ ሲጎበኙ ያገኘናቸው አሜሪካዊው ጄፍ ማዲሰን፤ የኢትዮጵያ የውበት መገለጫዎች የበዙና የሚያስደንቁ ናቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባ የአንድነት ፓርክን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ፓርኮችም የከተማዋ የውበት መገለጫዎችና ምቹ የመዝናኛ ሥፍራዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።


 

የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ የእንጦጦ ፓርክ እና ሌሎችም የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ተገንብተው ለጎብኝዎች ክፍት መደረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም