ቀጥታ፡

በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ልማትና የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ አህጉራዊ ትብብር በመፍጠር መሥራት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 03/2016 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ልማትና የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች በመደገፍ አህጉራዊ ትብብር በመፍጠር መሥራት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የመጀመሪያው የአፍሪካ የተማሪዎች የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ውድድር ተጠናቋል።

በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ47 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 3 ሺህ 700 ተወዳዳሪዎች ከ500 በላይ የፈጠራ ሃሳቦች ቀርበዋል።


 

በመድረኩም የቱኒዚያና ካሜሮን ተወዳዳሪዎች በጋራ የኦቲዝም ታማሚዎች ጋር በተሻለ መግባባት የሚያስችል መተግበሪያ ይዘው በመቅረብ አሸናፊ ሆነው የ10 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል።

የናሚቢያና አልጄሪያ ተወዳዳሪዎች ደግሞ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያሳልጡ መተግበሪያዎችን በማበልጸግ በቅደም ተከተል 2ኛ እና 3ኛ በመውጣት የ6 ሺህ እና የ4 ሺህ ዶላር ተሸላሚዎች ሆነዋል።

በማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የፈጠራ ሥራዎቹ  የአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንዲፋጠን በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።

አፍሪካ በበርካታ እምቅ ኃብቶች የታደለች አህጉር መሆኗን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አልቻለችም ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የአህጉሪቷን እድገትና ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የፈጠራና  ቴክኖሎጂ እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ባለልዩ ተሰጥዖ ባለቤት ወጣቶችን ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየሁ ማሞ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት የቴክኖሎጂ ፈጠራና ልማት የአገራት የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቱዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የዘመኑ ትኩረት በመሆኑ ኢትዮጵያም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የቱኒዚያ እና የካሜሮን እንዲሁም የናሚቢያ ተወዳዳሪዎች አፍሪካውያን ወጣቶች እርስ በርስ ልምድ በመለዋወጥ ለአህጉራዊ ልማትና እድገት መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም