የኖርዲክ ብላክ ቴአትር ቡድን አባላት አዲስ አበባ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኖርዲክ ብላክ ቴአትር ቡድን አባላት አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 3/2016 (ኢዜአ) ፦ የኖርዲክ ብላክ ቴአትር ቡድን አባላት የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለማቅረብ አዲስ አበባ ገባ።
ቡድኑ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊና ሚኒስትር ደኤታዎች አቀባበል አድርገውለታል።
የቴአትር ቡድኑ በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት 10 ቀናት በተለያዩ ቦታዎች የኪነጥበብ ሥራዎችን የሚያቀርብ ሲሆን የቡድኑ አባላትም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በጎፈቃደኛ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ ዋን ላቭ ቱር ኤንድ ትራቭል፣ በኖርዌይ ኦስሎ የኢትዮጵያ የክብር ቆንጽላና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅንጅት በሰሩት ሥራ ነው ተብሏል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ ሌንሳ መኮንን በዚሁ ጊዜ፤ ቡድኑ ወደ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
የቡድን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሀገሪቱ የአፍሪካ የኪነ ጥበብና ባህል ማዕከል መሆኗን ያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኖርዌይ የኢትዮጵያ የክብር ቆንጽላና የኢትዮ-ኖርዌይ የንግድ ምክር ቤት ተጠሪ ሰላማዊት ጅማ በበኩላቸው፤ የቴአትር ቡድኑ አባላት በብሄራዊ ቴአትር፣ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትና ሌሎችም ቦታዎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ያቀርባሉ ብለዋል።
የቡድኑ ጉብኝት በኢትዮጵያና ኖርዌይ መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ከማጠናከር ባሻገር ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅና ለገጽታ ግንባታ ያለው ፋይዳ የላቀ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የቡድኑ አባላት ለኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ልምዳቸውን የሚያጋሩበት መርሃ ግብር እንደሚኖር ጠቁመው፤ ይህም ለዘርፉ እድገት አወንታዊ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
የኖርዲክ ብላክ ቴአትር ቡድን ተወካይ ክሊፍ ሙስታሽ በበኩላቸው የሥልጣኔ መነሻ የሆነችውን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ኖርዲክ ብላክ ቴአትር ከ31 ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1992 በኖርዌይ የተመሰረተ የቴአትር ቡድን ነው።