ቀጥታ፡

የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲ መቋቋም አፍሪካውያን ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድሃኒቶችን በዘላቂነት እንዲያገኙ ያግዛል-ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 3/2016 (ኢዜአ) ፦የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲ መቋቋም የአህጉሪቱ ህዝብ ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድሃኒቶችን በዘላቂነት እንዲያገኙ የሚያግዝ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

በፈረንጆቹ 2019 በአዲስ አበባ በተካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ በህብረቱ ጥላ ስር አህጉራዊ የመድሃኒት ኤጀንሲ ለማቋቋም ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።

ዓላማውም ከመድሃኒት ምርቶች ቁጥጥር ስርዓት ጋር በተያያዘ በአህጉሩ ቅንጅታዊ አሰራርን ለመዘርጋት ሲሆን፤ ኤጀንሲውን ለማቋቋም የወጣውን ስምምነት እስካሁን 26 አገራት አጽድቀውታል።

ከህብረቱ አባል ሀገራት መካከል ቢያንስ 15ቱ ስምምነቱን ካጸደቁት ኤጀንሲው ወደ ስራ እንደሚገባም ታውቋል።

ኢትዮጵያም ይህን ስምምነት ከራሷ ህግ ጋር በተጣጣመ መልኩ አዋጅ አድርጋ ለማውጣት የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገች ነው።


 

በዚሁ መሰረት የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ስምምነት ፋይዳን በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማትና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  አባላት  ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድሃኒቶችን ማቅረብ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች አሉ።

በዚህ ረገድ የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲ መቋቋም ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድሃኒቶችን ለህብረተሰቡ በዘላቂነት ለማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ኤጀንሲው ጠንካራና የተቀናጀ የቁጥጥር ስርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ አገራዊ የመድሃኒት ቁጥጥር ተቋማትን ከማጠናከርና አቅማቸውን ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

በአህጉር ደረጃ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን ከሟሟላት ባለፈ ድንበር ዘለል አሰራርን ለመፍጠር እንደሚረዳም ነው ያስገነዘቡት።


 

የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመድሃኒት፣ የህክምና መሳሪያና ሌሎች የጤና ግብዓቶች ጥራትና ቁጥጥር እንዲጠናከር ከአህጉሪቱ አገራት ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኤጀንሲው ወደ ስራ ሲገባ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በመድሃኒቶች ጥራትና ቁጥጥር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀነስ የድንበር ላይ ቁጥጥርን እንደሚያጠናክር ጠቅሰዋል።

አገራቱ የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የቁጥጥር አቅማቸውን ለማጎልበት ያግዛቸዋል ብለዋል።

የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲ በአህጉሩ ያለውን ባህላዊ መድሃኒቶች ከዘመናዊው ጋር በማስተሳሰር የመድሃኒት ተደራሽነትን ለማስፋት እንደሚያግዝም ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም