ኅብረተሰቡ ጤናማ የኑሮ ዘይቤ በመከተል የስኳር ሕመምን ሊከላከል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኅብረተሰቡ ጤናማ የኑሮ ዘይቤ በመከተል የስኳር ሕመምን ሊከላከል ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 3/2016 (ኢዜአ) ፦ኅብረተሰቡ ጤናማ የኑሮ ዘይቤ በመከተል በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የስኳር ሕመም መከላከል እንዳለበት የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበር አሳሰበ።
የዓለም የስኳር ሕመም ቀን በነገው ዕለት "ስለ ስኳር ሕመም አጋላጭ ሁኔታዎችን ይገንዘቡ፣ ምላሹንም ይወቁ?" በሚል መሪ ኃሳብ ይከበራል።
በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከ12 በመቶ በላይ የሚሆነው የቅድመ ስኳርና የስኳር ሕመም እንዳለበት በቅርቡ በተካሄደ ጥናት መረጋገጡን የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበር ገልጿል።
ከዚህም ውስጥ 3 ነጥብ 2 በመቶው ከተረጋገጠ የስኳር ሕመም ጋር የሚኖሩ ሲሆን 9 ነጥብ 1 በመቶው ደግሞ በቅድመ ስኳር ህመም ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነው ማኅበሩ የጠቆመው።
የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ፤ የስኳር ቀንን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የስኳር ሕመም እየጨመረ ነው ብለዋል።
በተለይም ሕጻናትና ወጣቶች ለስኳር ሕመም የመጋለጥ ምጣኔያቸው መጨመሩን ነው የጠቆሙት።
ይህንንም ተከትሎ ኅብረተሰቡ ጤናማ የኑሮ ዘይቤ በመከተል ለስኳር ሕመም ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚገባ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ጠቁመዋል።
በተጓዳኝም ከልክ ያለፈ ውፍረትን መቀነስ፤ ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ ለደም ግፊት የሚያጋልጡ አስቻይ ሁኔታዎችን መቀነስ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
ቅባት ያለው ምግብ እንዲሁም ጣፋጭ ምግቦችን መቀነስ እንደሚገባም ምክረ ኃሳብ ሰጥተዋል።
የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ለስኳር ሕመም ተጋላጭነትን ይቀንሳል ያሉት ፕሬዝዳንቱ እድሜያቸው 45 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ግለሰቦች በመደበኛነት የስኳር ሕመም መመርመር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን በበኩላቸው፤ የስኳር ሕሙማን ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን አረጋግጠዋል።
ይህንንም ከግምት በማስገባት ኅብረተሰቡ ለስኳር በሽታ ተጋላጭ እንዳይሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጎን ለጎንም ለስኳር ሕሙማን አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።